የትግራይ ግጭት፡ አምስቱ የትግራይ ክልል አስተዳደር ተግዳሮቶች

ትግራይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በህወሓት ይመራ የነበረው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ከስልጣን ከተነሳ በኋላ፣ በፌደራል መንግስት የተቋቋመውን ግዝያዊ አስተዳደር ዶክተር ሙሉ ነጋ ሲመሩት ቆይተዋል።

ከቀናት በፊት ደግሞ የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር አብርሃም በላይ፣ ዶክተር ሙሉ ነጋን ተክተው ተሹመዋል።

ከአምስት ወራት በላይ ትግራይን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ዶክተር ሙሉ ነጋን፣ ለምን በዶክተር አብርሃም መተካት እንደተፈለገ የተሰጠ ማብራርያ የለም።

የትግራይ ክልል የህዝብ እና መንግስት ግንኙነት ምክትል ሃላፊ የነበሩት አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ እና የትግራይ ኮንስትራክሽን፣ መንገድና እና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት ኢንጂነር አሉላ ሃብተአብ ከመጋቢት 12/2013 ጀምረው ከስልጣናቸው መነሳታቸው ይታወሳል።

ቀደም ሲልም የመቀለ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ አታኽልቲ ሃይለስላሰም ከሃላፊነታቸው ለቅቀዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፡ "የህዝብ ጥያቄ መመለስ እንጂ ሰዎች መቀያየር ለውጥ አያመጣም" ሲሉ ተናግረዋል።

ለመሆኑ የግዝያዊ አስተዳደሩ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምን ምን ናቸው?

የፀጥታ እና የሰላም ሁኔታ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ 'ህግ የማክበር ዘመቻው' እንዳበቃ ቢገልፁም በተለያዩ የትግራይ ኣካባቢዎች ለስድስት ወራት ውግያ እየተካሄደ እንደሆነ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አገራት ይገለፃል።

በዚህ ምክንያት በመቀለ እና ሌሎች ከተሞች በተለያዩ ወንጀሎች በእስር ላይ የነበሩ ሰዎች ተለቅቀው በዝርፍያ እና ግድያ የመሳሰሉ ወንጀሎች መሰማራታቸውን እና በዚህም ህብረተሰቡን ሰላም እንዳሳጡት በሰፊው ይነገራል።

የፌደራል መንግስት ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል የዕለት እርዳታ ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ እንዳለ ቢነገርም በፀጥታ ችግር ምክንያት ከከተማ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች መድረስ ከባድ ሆኗል ይላሉ።

በዚህ ሳምንት ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ባወጣው ሪፖርት ላይ ወደ አብዛኛው የትግራይ አካባቢዎች እና የገጠር ቦታዎች መድረስ አለመቻሉን እና "በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች እርዳታ እያገኙ አለመሆኑን" ገልጿል።

የፌደራል መንግሥት ግን በትግራይ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ ወደ ቀድሞው መረጋጋት እየተመለሰ መሆኑን በሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ይገልፃል።

አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ ግን ግዜያዊ አስተዳደሩ እስከ አሁን በትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ማረጋገጥ እንዳልቻለ እና ይህን ለማድረግ ደግሞ በቀጣይነት ትልቅ ስራ እንደሚቀረው ይናገራሉ።

የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ለቅቆ አለመውጣት

የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ባላቸው ተሳትፎ እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ ፆታዊ ጥቃት እና ዝርፍያ መሳተፋቸው ተገልጾ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይወነጀላሉ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተለያየ ጊዜ ባወጡት ሪፖርት የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ንፁኀን ዜጎችን መግደላቸውን በመግለጽ ሪፖርት አድርገዋል።

ባለፈው መጋቢት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለመጀመርያ ግዜ የኤርትራ ሰራዊት የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው መግባታቸውን በመግለጽ የኤርትራ መንግሥት ሰራዊቱን ለማስወጣት መስማማቱን ገልፀው ነበር።

አሜሪካም የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ በአስቸኳይ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ጠይቃለች።

የዓረና ትግራይ ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ ይህንን ጉዳይ ካነሱት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዝሃን በሰጡት መግለጫ ምክንያት ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ ይገልፃሉ።

አቶ አምዶም የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል መገኘት ጊዝያዊ አስተዳደሩ በተለያዩ ኣካባቢዎች ባካሄዳቸው ህዝባዊ መድረኮች በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።

የትግራይ ግዛታዊ አንድነት ጥያቄ

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በመጋቢት ወር መጀመርያ በምዕራባዊ ትግራይ በህዝብ ላይ "የዘር ማፅዳት" ወንጀል እንደተፈፀመ ገልፀው ነበር።

ብሊንከን አክለውም የአማራ ክልል ሃይሎች ከአካባቢው በአስቸኳይ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ግን ለዚህ ጥሪ "ውስጣዊ ጉዳይ ነው" በማለት አልተቀበለውም፤ የአማራ ክልል መንግሥትም ቢሆን ይህንን በመቃወም መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

በመግለጫው "በሃይል የተወሰደ መሬት በሃይላችን አስመልሰናል" የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

አብዛኞቹ የትግራይ ግዝያዊ አስተዳደር ባለስልጣኖች ጉዳዩን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ ስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ ከኤርትራ ሰራዊት እኩል 'በአማራ ክልል የተወሰደ መሬት ይመለስ' የሚል ዋነኛው የትግራይ ህዝብ ጥያቄ መሆኑ ይናገራሉ።

"መሬታችን አስወርራችሁ ምንድነው እያስተዳደራችሁ ያላችሁት? ትግራይ ይህቺ ናት እንዴ?" የሚል ትልቅ ጥያቄ በተደጋጋሚ ከህዝብ እንደሚነሳ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የህክምና ማዕከላት ውድመት

70 በመቶ የሚሆኑ የትግራይ የህክምና ማዕከላት እንደወደሙ እና የህክምና መሣርያዎችም እንደተዘረፉ ድንበር የለሹ የሃኪሞች ቡድን ባለፈው መጋቢት ወር ባወጣው ሪፖርት መግለፁ ይታወሳል።

በደረሰው ጉዳት ምክንያት በጣም ጥቂት ሠራተኞች ብቻ በሥራ ገበታቸው እንደሚገኙ እና በአንዳንድ ማዕከላት ደግሞ አንድም ሠራተኛ እንደሌለ ማህበሩ ገልፆ ነበር።

መንግስት አብዛኛዎቹ የወደሙ ማዕከላት ጥገና እንደተደረገባቸው እና ወደ ሥራ እንደተመለሱ ይገልፃል፤ ቢሆንም ይህ መንግስት ዘገባ በሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አልተደገፈም።

ድንበር የለሹ የሃኪሞች ቡድን በዚህ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ደግሞ፣ አባላቶቹ ወደ አንዳንድ አካባቢዎች በሄዱበት ግዜ የጤና ተቋማት ወድመው እና ተዘርፈው እንዳዩ እና የአካቢዎቹ ነዋሪዎች አስፈላጊ ህክምና እንዳላገኙ አረጋግጧል።

ስደት እና ሰብአዊ ቀውስ

ጦርነቱ ተከትሎ ብዙዎች ቀያቸው ጥለው የተሰደዱ ሲሆኑ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከምዕራብ ትግራይ እየተፈናቀሉ እንደሆኑ ዘገባዎች ያመላክታሉ።

በአጠቃላይ ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በመቀለ፣ ሽረ፣ አክሱም እና ዓድዋ ከተሞች በትምህርት ቤቶች እና ያላለቁ ህንፃዎች ውስጥ ይገኛሉ።

የድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ሃላፊ ሶፊ ማዴን "በቂ መጠለያ እና ምግብ የላቸውም፤ በተለይም ንፁህ የመጠጥ ውሃ አያገኙም" በማለት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ድርጅቱ በዚህ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት በተለይ በትግራይ ገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች መሰረታዊ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ አሳውቋል።

በጦርነቱ ምክንያት ከባድ የምግብ እጥረት አጋጥሞ እንደሚገኝ እና በተለይም ህፃናት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ከሚገኙት መካከል እንደሆኑ ይገለፃል።

ሴቭ ዘ ቺልድረን የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ማህበር ባወጣው ሪፖርት 5 ሺ የሚሆኑ ህፃናት በጦርነቱ ከቤተሰቦቻቸው እንደተለያዩ አሳውቋል።