ባይደንን ከሞት ያተረፏቸው አፍጋናዊ አስተርጓሚ አሜሪካ ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Safi Rauf/Human First Coalition
ጆ ባይደን ሴናተር እያሉ አፍጋኒስታን ውስጥ ከአደጋ ያተረፏቸው አስተርጓሚና ቤተሰቦቻቸው ጓዛቸውን ጠቅልለው ከሃገራቸው መውጣታቸው ተሰምቷል።
ጊዜው 2008 ነበር። በፈረንጆቹ። የአሁኑ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንና ሌሎች ሴናተሮችን የያዘ ሄሊኮፕተር በከባድ አየር ምክንያት ከአንዲት የአፍጋኒስታን መንደር ለማረፍ ይገደዳል።
ሥፍራው ለወትሮው የበረዶ ጥጥ የሚዘንብበትና ታጣቂዎች ጥቃት አከታትለው የሚያደርሱበት ነው።
አማን ካሊል በአሜሪካ መንግሥት ተቀጥረው ከሚሠሩ አፍጋናዊያን መካከል ነበሩ። አሜሪካዊያኑን ሴናተሮች በመኪናቸው አሳፍረው ወደ ድብቅ ሥፍራም ወስደዋል።
አስተርጓሚው ከባለፈው ነሐሴ ጀምሮ ወደ አሜሪካ የሚያስገባ ቪዛ ማግኘት አቅቷቸው ላይ ታች ሲኳትኑ ቆይተዋል።
ነገር ግን አሁን በታሊባን ቁጥጥር ሥር ያለችውን ሃገራቸውን እንደ ሌሎች በርካታ ሺህ አፍጋናዊያን ወደኋላ ጥለው ወጥተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ፤ አስተርጓሚው ካሊልና ቤተሰቦቻቸው ከአፍጋኒስታን በሰላም ወጥተዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"አስተርጓሚው ከአፍጋኒስታን የወጡት በአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ ነው። ይህ ጉዳይ እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉልን ምስጋና እናቀርባለን" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ካሊል የአሁኑን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጨምሮ ሴናተር ቻክ ሄግልና ሴናተር ጆን ኬሪን በአካል ካገኙ ከ13 ዓመታት በኋላ ወደ አሜሪካ የሚያስገባቸውን ቪዛ ለማግኘት እየጣሩ ነው።
አሜሪካ አፍጋኒስታንን ለታሊባን ጥላ ከወጣች በኋላ ካሊል ፕሬዝደንት ባይደን እንዲያድኗቸው ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም።
እሳቸውንና ሚስታቸውን እንዲሁም አምስት ልጆቻቸውን ከአፍጋኒስታን እንዲያስወጣቸው በሲኤንን ጥሪ ያቀረቡት ካሊል "አምናቸዋለሁ። ሁሉን የማድረግ አቅም እንዳላቸው አምናለሁ" ብለው ነበር።
ባለፈው መስከረም ስለ አቶ ካሊል ጉዳይ የተጠየቁት የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ አስተርጓሚው ላደረጉት ነገር አመስግነው መንግሥታቸው ሰውዬው ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ቁርጠኛ መሆኑን መናገራቸው አይዘነጋም።
ካሊል አሁን ከአፍጋኒስታን ወጥተው ፓኪስታን እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ሂዩማን ፈርስት ኮአሊዥን የተሰኘውና አሁን ፓኪስታን የሚገኙ 200 አፍጋናዊያንን ከካቡል ያስወጣው የተራድዖ ድርጅት የባይደን አስተርጓሚ በሕይወት በመውጣታቸው ደስተኛ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።
አሜሪካ በአፍጋኒስታን በኢራቅ በነበሩት ጦርነቶች አሜሪካዊያን ወታደሮችን በማስተርጎምና በሌሎች መስኮች ላገዙ ዜጎች ልዩ ቪዛ አዘጋጅታለች።
ካሊል ወደ ዋሺንግተን የሚያስገባቸውን ቪዛ አግኝተው ወደ አሜሪካ ያቀኑ እንደሆነ እስካሁን ግልፅ አይደለም።
ከፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ 70 ሺህ አፍጋኒስታናዊያን በአሜሪካ እርዳታ ሃገራቸውን ለቀው ወጥተዋል።












