ናይጄሪያ ውስጥ በባህላዊ መድኒት ምክንያት 10 የአንድ ቤተሰብ አባላት ሞቱ

በምዕራዊ ናይጄሪያ በምትገኝ ክዋራ በተባለች ግዛት አንድ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ 10 ሰዎች ባህላዊ መድኃኒት ነው በሚል ከተለያዩ እጸዋት የተቀመመ መድኃኒት ከጠጡ በኋላ ህይወታቸው ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
ይህ ሞትን ያስከተለ ክስተት የተፈጠረው ሁለት ተጠርጣሪዎች በአንድ መንደር ውስጥ እግሯን ያመማት አንዲት ሴት ከእጸዋት የተዘጋጀው ውህድ ከህመሟ እንደሚፈውሳት በመግለጽ እንድትወስድት ያግባቧታል።
ነገር ግን ግለሰቧ መድኃኒቱን ስትወስድ በሽታው ወደቀሪው የቤተሰቧ አባላት እንዳይመዛመት ሁሉም በባህላዊውን መድኃኒት መውሰድ እንዳለባቸው ተነግሯት ነበር።
በዚህም ምክንያት አስር የቤተሰቡ አባላት መድኃኒቱን እንእንዲጠጡ ተደረገ። ታዲያ ውጤቱ ሞትን አስከተለ።
የክዋራ ግዛት የፖሊስ ቃል አቀባይ ኦካሳንሚ አጃይ ትላንት ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ባህላዊ መድኃኒቱን የወሰዱት ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ህይወት እንዳለፈ ተናግረዋል።
በዚህም ሳቢያ ዋነኛዋን ታማሚ ጨምሮ "አስር የቤተሰቡ አባላት በጠጡት ውህድ ምክንያት ሞተው ተገኝተዋል" ሲሉ የፖሊስ ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ፖሊስ ጨምሮም በባህላዊው መድኃኒት ሰበብ ከሞቱት ከቤተሰቡ አባላት መካከል ትንሽ ዕድሜ ያለው የሁለት ዓመት ህጻን ሲሆን ትልቁ ደግሞ የአርባ ዓመት ጎልማሳ ነው ተብሏል።
ፖሊስ ሁለቱን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾል። ተጠርጣሪዎቹ በገጠራማው ስፍራ በሚገኘው ማኅበረሰብ ውስጥ የሚታወቁ ባህላዊ መድኃኒት ቀማሚዎች መሆን አለመሆናቸው ግን ገና አልተረጋገጠም።
በርካታ ናይጄሪያውያን በተለይም በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩት በእውቀትና ገንዘብ ማጠር እንዲሁም በባህላዊ እምነቶች ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎችን ፈውስ ለማግኘት ቁጥጥር በማይደረግባቸው ባህላዊ ህክምናና መድኃኒቶችን ይጠቀማሉ።
የአገሪቱ የጤና ሥርዓትም ቢሆን በበርካታ ችግሮች ውስጥ ያለ ነው ተብሏል።












