በግሪክ የኦርቶዶክስ ጳጳሳት ላይ የአሲድ ጥቃት የፈፀሙት ቄስ ተያዙ

በፔትራኪ ገዳም ፖሊስ ሲመረምር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በግሪኳ መዲና አቴንስ በሰባት የግሪክ ኦርቶዶክስ ጳጳሳት ላይ የአሲድ ጥቃት የፈፀሙት ቄስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው በትናንትናው ዕለት ረቡዕ ሲሆን የ36 አመቱ ቄስ ከዚህ ቀደም ካጠፉት ጥፋት ጋር ተያይዞ መፈፀም ስላለበት መጣጣኝ ቅጣት በተመለከተ እየተካሄደ ባለ ስብሰባ መሆኑንም ፖሊስ አመላክቷል።

ሶስቱ ጳጳሳት አሲዱ በአብዛኛው የተደፋባቸው ፊታቸው ላይ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በሆስፒታልም ህክምና እየተደረገላቸው ነው።

ቄሱ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እጃቸው አለበት በሚልም ነው ቤተ ክርስቲያኗ ስትወያይ የነበረው።

ግለሰቡ ከሶስት አመት በፊት 1.8 ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ ይዘው መገኘታቸውን ተከትሎ የቅስና ማዕረጋቸው ሊነጠቅ ይገባል በሚልም ነው ጳጳሳቱ እየተወያዩ የነበረው ብሏል የአገሪቱ ሚዲያ

በአሁኑ ወቅት ከቤተ ክርስቲያኗ ሊባረሩ እንደሚችሉም አና የተባለው የዜና ወኪል አስነብቧል።

ስብሰባው እየተደረገ የነበረው በመካከለኛው አቴንስ በሚገኝ ፔትራኪ ገዳም ሲሆን ቄሱም ትልቅ ጠርሙስ አሲድ ገዝተው ወደ ስፍራው መውሰዳቸውን ታ ኒያ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።

ቄሱን ከገዳሙ በር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የገዳሙ ጥበቃም በአሲዱ ቃጠሎ ደርሶበት ለህክምና ሆስፒታል ተወስዷል ተብሏል።

የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ቫሲሊስ ኪኪሊያስ ጥቃት የደረሰባቸውን ጳጳሳት የጎበኙ ሲሆን አንደኛው ግለሰብ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ወደ ሌላ ሆስፒታል እንደሚዛወሩም ተገልጿል።

የግሪክ ፕሬዚዳንት ካትሪና ሳኬላሮፑሎ ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ክይራኮስ ሚስታኮስ ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቴንስ ኢሮንሞስ ሁለተኛ ጋር ተወያይተዋል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተፈፀመው ጥቃት ከልባቸው እንዳዘኑ ገልፀው ለፓትርያርኩም "መንግሥታቸው ጥቃት ለደረሰባቸው ጳጳሳት ከህመማቸው በአስቸኳይ እንዲያገግሙ አስፈላጊውን የህክምና እርዳታም እንደሚለግሱ መናገራቸው ተዘግቧል።