በጣልያን የጠፋ ጨቅላ ዘገባን ሊሰራ የተላከው ጋዜጠኛ ህፃኑን ማግኘቱ ተነገረ

ህፃኑ በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተይዞ

የፎቶው ባለመብት, CNSAS/ Twitter

በጣልያን አንድ የጠፋ ጨቅላ ዘገባ ሊሰራ የተላከው ጋዜጠኛ ህፃኑን እንዳገኘው ተነግሯል።

ልጁ ከቤቱ ጥቂት ኪሎሜትር ራቅ ብሎ እንደተገኘም ተገልጿል።

ሁለት አመት ያልሞላው ይህ ጨቅላ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው ሰኞ ምሽት መኝታ ክፍሉ ውስጥ ሲሆን በነገታውም ቤተሰቦቹ ጠፍቷል ሲሉ ለፖሊስ ሪፖርት አድርገዋል።

ጁሴፔ ዲ ቶማሶ በአካካቢው በሚገኝ ሸለቆ ድምፅ መስማቱን ተከትሎም ነው በትናንትናው ዕለት የተገኘው።

ህፃኑ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን በጥሩ ጤንነትም ላይ ነው ተብሏል።

ኒኮላ ታንቱርሊ የተባለው ህፃን ሌሊት ላይ እንደነቃና ከቤቱም ወጥቶም እንደሄደም ይታመናል።

ልጁን ለመፈለግ ሄሊኮፕተር እንዲሁም ፖሊስ፣ የእሳት አደጋ ሰራተኞች፣ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን ጨምሮ 1 ሺህ ሰዎች ፍሎረንስ አካባቢ በምትገኘው ፓላዙኦሎ ሱል ሴኒዮ መንደር መሰማራታቸውን የአካባቢው ከንቲባ ተናግረዋል።

ለጣልያን መንግሥት ሚዲያ የሚሰራው ጁሰፔ ዲ ቶማሶ ለቅሶ የሚመስል ድምፅ መስማቱን ተከትሎም ነው ለፖሊስ የተናገረው።

የአካባቢው ፖሊስም ምርመራም ወደ ሸለቆው ወረድ ብለው ምርመራ በሚያደርጉበትም ወቅት " ለቅሶው እየጎላ መጣ እናም እንስሳ የሚወጣ መስሎን " ነበር በማለት የፖሊስ ኃላፊው ዳኒሎ ሲካሬሊ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

"በረዣዥም ሳር ከተሸፈነው ሸለቆ ግን እየዳኸ የወጣው ኒኮላ ነበር። ማማ ብሎም ተጣራ። በጣም የሚያስደስት ስሜት ነው"በማለት ተናግረዋል።

ኒኮላ ለምርመራ ወደ ህክምና ማዕከል የተወሰደ ሲሆን ቀለል ካሉ ጉዳቶች በስተቀር ይህ ነው የሚባል ጉዳት እንዳልደረሰበት የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

"መቆጣጠር የማልችለው ስሜት ነው የተሰማኝ። አሁንም እየተንቀጠቀጥኩ ነው" በማለት ጋዜጠኛው ለአንሳ የዜና ወኪል ተናግሯል።