10 ወለደች የተባለችው የደቡብ አፍሪካዊቷ ታሪክ ሃሰተኛ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, African News Agency (ANA)
በያዝነው ወር ደቡብ አፍሪካዊቷ ጎሲዬም ሲትሆል 10 ልጆችን በመውለድ ክብረ ወሰን እንዳስመዘገበች ቢዘገብም የግለሰቧ ታሪክ ሃሰተኛ መሆኑን አንድ ይፋዊ ምርመራ አስታወቀ።
በጋውቴንግ አውራጃ የሚገኝ ሆስፒታሎች ውስጥ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ልጆች ስለመወለዳቸው አልተመዘገበም ይላል የክልሉ መንግስት፡፡
የህክምና ምርመራዎች እንደሚያሳዩት ሲትሆል በቅርቡ እርጉዝ እንዳልነበረችም ገልጸዋል፡፡
ታሪኳ ይፋ መውጣቱን ተከትሎ የ 37 ዓመቷ ግለሰብ የአዕምሮዋን ጤንነት ክትትል እተደረገበት ሲሆን ድጋፍ ይሰጣታልም ተብሏል፡፡
ይህን መሰሉ ታሪክ ለምን እንደተፈበረከ መግለጫው በዝርዝር አልገለጸም፡፡
ታሪኩን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው በኢንዲፔንደንት ኦንላይን ባለቤትነት የሚተዳደረው ፕሪቶሪያ ኒውስ ነው።
ሚዲያው አሁንም ቢሆን መረጃው ትክክል ነው በሚልም እየተከራከረ ይገኛል።
ሲትሆል ልጆቹን ሰኔ 7 ፕሪቶሪያ በሚገኘው ስቲቭ ቢኮ አካዳሚክ ሆስፒታል ተገላግላለች ብሎ የሆስፒታሉ ሠራተኞችበቂ ዝግጅት አላደረጉም በሚልም ዘገባው ይከሳል።
ሆስፒታሉን እና የክልሉ ጤና ባለሥልጣናትን የህክምና ቸልተኝነትን ለመሸፈን ጥረት አድርገዋል ሲልም አስነብቧል፡፡
መግለጫው በበኩሉ "እነዚህ ክሶች ሀሰተኛ፣ ተጨባጭነት የጎደላቸው እና የስቲቭ ቢኮ አካዳሚክ ሆስፒታል እና የጋውቴንግ አስተዳደርን መልካም ስም ለማጠልሸት ብቻ የተዘጋጁ ናቸው" ብሏል፡፡
በፕሪቶሪያ ኒውስ ዋና አዘጋጅ ፒየት ራምፔዲ እና ኢንዲፔንደንት ኦንላይን ላይም ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳልም ብተሏል፡፡
ታሪኩ ከየት መጣ?
ስድስት ዓመት የሞላቸው መንትዮች ያሏት ሲትሆል እና የትዳር አጋሯ ተቦሆ ጾቴሲ የሠራተኛው መደብ በሚኖሩበት በጆሃንስበርግ አቅራቢያ በምትገኘው ጋውቴንግ አውራጃ ቴምቢሳ ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡
እንደ ኢንዲፔንደንት ኦንላይን መረጃ ከሆነ በታህሳስ ወር የተዋወቁ ሲሆን ዘገባውን ከሰራው ራምፔዲ ጋርም በተመሳሳይ ቤተ እምነት ይሳተፋሉ፡፡
በግንቦት ወር ስምንት ሕፃናትን እንደሚወልዱ የተናገሩትን ባልና ሚስትንም ይኸው ሚዲያ ቃለ መጠይቅ አድርጓል ተብሏል። ሲትሆል በአንድ ፎቶግራፍ ላይ ሆዷ በጣም ገፍቶ ያሳያል፡፡
አስገራሚውን የ 10 ሕጻናት መወለድ ባለቤቷን ጾቴሲን በመጥቀስ ፕሪቶሪያ ኒውስ ሰኔ 8 ይፋ አደረገ፡፡
በኋላም በኮሮናቫይረስ እገዳዎች ምክንያት ሆስፒታሉ መግባት እንዳልተፈቀደለት የትዳር አጋሩ የጽሑፍ መልእክት ደርሶኛል ብሏል፡፡
ራምፔዲም አስር ስለ መውለዷ ሲዘግብ በባለቤቷ የዋትስአፕ መልእክቶች መረጃ ላይ የተመሠረተም ቢሆንም ስለታሪኩ ሆስፒታል ገለልተኛ ማረጋገጫ አላገኘም፡፡
የአካባቢው ከንቲባ ስለጉዳዩ ማረጋገጣቸውን ተከትሎ ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች የዜና አውታሮች ታሪኩን ዘገቡት።
በኋላ ግን ፖለቲከኛው የቤተሰባቸው ቃል ላይ ብቻ እንደተመሠረቱ እና ሕጻናቱን የጎበኘ የለም ብለዋል የመንግሥት ቃል አቀባይ፡፡
ዜናው ይፋ ከሆነ በኋላ ብዙዎች ለባለትዳሮቹ ድጋፍ እያደረጉ ነበር። "ቴምቢሳ 10" የሚል ስም ላገኙት ልጆች የኢንዲፔንደንት ኦንላይን ሊቀመንበር ኢክባል ሰርቪ የሰጡትን 70,000 ዶላር ጨምሮ ብዙዎች ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ፕሪቶሪያ ኒውስ ህጻናቱ የተወለዱበትን ሆስፒታል በመጀመሪያ ይፋ ማድረግ ባለመቻሉ እና በጋውቴንግ ያሉ ሆስፒታሎች ታሪኩ በሆስፒታላቸው አለመፈጸሙን በተከታታይ ወጥተው በመናገራቸው ታሪኩ ጥርጣሬ ውስጥ ወደቀ።
ኢንዲፔንደንት ኦንላይን ልጆቹ ተወለዱበት ከተባለበት ከአስር ቀናት በኋላ የስቲቭ ቢኮ አካዳሚ ሆስፒታልን ወንጅሏል።
ባልና ሚስቱ ከዚህ ክስተት በኋላ የተለያዩ ይመስላሉ። ጾቲሲ ሚስቱ መጥፋቷን ሪፖርት ካደረገ ከሳምንት በኋላ ሰዎች ልገሳቸው እንዲያቆሙ ጠይቋል።
ሲትሆል በበኩሏ በህጻናቱ ምክንያት በሚሰበሰበው በገንዘብ ተጠቃሚ ለመሆን አስቧል ስትል መክሰሷን ፕሪቶሪያ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ማህበራዊ አገልግሎት ሠራተኞች ሲትሆልን ተከታትለው ካገኙ በኋላ ባለፈው አርብ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል መግባቷን የጋውቴንግ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
ኒውስ 24 ያገኘው በድብቅ ማስታወሻ ራምፔዲ ታሪኩን እንደ ምርመራ ዘገባ መውሰድ ነበረብኝ በሚል ታሪኩ በድርጅቱ ላይ ያስከተለውን "የስም ማጉደፍ" ተከትሎ ኢንዲፔንደንት ኦንላይንን ይቅርታ መጠየቁን ይገልጻል፡፡












