የዱባይ ገዥ ልጅ ልዕልት ላቲፋ ስፔን ውስጥ እንዳለች የሚያሳይ ፎቶ ወጣ

የኢንስታግራሙ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Instagram

ለወራት ስላለችበት ሁኔታ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቀው የዱባይ ገዥ ልጅ ልዕልት ላቲፋን የሚያሳይ ፎቶግራፍ ብቅ ብሏል።

የኢንስታግራም ምስሉ ልዕልት ላቲፋ ከጓደኛዋ ጋር በማድሪድ አየር ማረፊያ ያለች ይመስላል ተብሏል፡፡

በየካቲት ወር ቢቢሲ በደረሰው በልዕልት ላቲፋ በተቀረጸ ቪዲዮ አንድ ቪላ ውስጥ ተይዛ እንደነበረች እና ለህይወቷ እንደምትፈራ ገልጻ ነበር፡፡

ቪዲዮውን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት በሕይወት መኖሯን "ተጨባጭ" ማረጋገጫ እንዲጠይቅ ምክንያት ሆነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ባለሙያዎችም "በአስቸኳይ" መፈታት አለባት ብለዋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ "በቤት ውስጥ እንክብካቤ እየተደረገላት ነው" ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

"መሻሻል እያመጣች ሲሆን በተገቢው ሰዓት ወደ ህዝባዊ ህይወት ትመለሳለች የሚል ተስፋ አለን" ብሏል መግለጫው፡፡

ፎቶው ምን ያሳያል?

ይህ የቅርብ ጊዜ ምስል በሲዮኔድ ቴይለር የኢንስታግራም ገጽ ላይ ተለጥፏል። ዱባይ ውስጥ የምትኖረው እና የረጅም ጊዜ ጓደኛዋ የሆነችው ቴይለር ከግንቦት አጋማሽ አንስቶ ልዕልት ላቲፋን ምስል ስትለጥፍ ሦስተኛው ጊዜ ነው፡፡

"ትልቅ የአውሮፓ እረፍት ከላቲፋ ጋር" ይላል ከስሩ ያለው ጽሑፍ፡፡ "የተለያዩ ቦታዎችን እየጎበኘን እየተዝናናን ነው" ይላል።

ሁለቱም ሴቶች የፊት መሸፈኛ ጭምብል አጥልቀው በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ ባራያስ አየር ማረፊያ ያሉ ይመስላል፡፡

ላቲፋ ነጻ ትሁን የሚለው ዘመቻ ተባባሪ መስራች ዴቪድ ሃይግ በላከው መግለጫ "ላቲፋ ፓስፖርት ስላላት፣ እየተጓዘች እና እየጨመረ የመጣውን የነጻነት ደረጃ ማየቴ ደስ ብሎኛል" ብሏል፡፡

ልዕልቷ ላቲፋ ነጻ ትሁን ቡድን አባላት በቀጥታ እንዳነጋገረች ገልጾ በዚህ ወቅት ተጨማሪ አስተያየት መስጠት እንደማይችል አክሏል፡፡

በግንቦት ወር ቴይለር በኢንስታግራም ዱባይ ውስጥ በሚገኝ የገበያ አዳራሽ እና በኋላም በከተማው ውስጥ ባለ ምግብ ቤት ልዕልት ላቲፋን የሚያሳዩ ሁለት ፎቶዎችን ለጥፋ ነበር፡፡

ላቲፋን ምን አገኛት?

ከ 25ቱ የሼክ ሞሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም ልጆች መካከል አንዷ የሆነችው ላቲፋ የካቲት 2018 ከዱባይ ለማምለጥ ሙከራ አደረገች፡፡

ከመሄዷ ጥቂት ቀደም ብላ በተቀረጸው ቪዲዮ ህይወቷ በጣም መገደቡን አስታውቃለች።

ከአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ ሀገሪቱን ለቅቄ አልተወጣሁም። ለመጓዝ፣ ለመማር እና መደበኛ ነገር ሁሉ ለማድረግ ብዙ እጠይቃለሁ። እነሱ ግን አይፈቅዱልኝም" ብላለች፡፡

የማምለጥ ሙከራዋ ግን አልተሳካም። የህንድ ውቅያኖስን አቋርጠው ለስምንት ቀናት በባህር ጉዞ ሲጓዙ ተይዘው ኮማንዶዎች ላቲፋን በኃይል ወደ ዱባይ መለሷት፡፡

በኋላም አባቷ ይህንን እንደ "የነፍስ አድን ተልዕኮ" እንደቆጠሩት ተናግረዋል፡፡

እአአ በየካቲት 2021 ቢቢሲ ፓኖራማ በልዕልት ላቲፋ በድብቅ በተቀረጹ ቪዲዮዎችን እና በውጭ ካሉ ወዳጆቻቸው ጋር በማነጋገር ዱባይ ከተመለሰች በኋላ መያዟ እና መታሰሯን ገልጻለች፡፡

መስኮቶቹና በሮቹ በተዘጉበት እና በፖሊስ ጥበቃ በሚደረግበት ቪላ ውስጥ የህክምና እና የህግ ድጋፍ ሳታገኝ ብቻዋን ተይዛ እንዳለችም ተናግራለች፡፡