ፈረንሳዊቷ ለበርካታ አመት ጥቃት ያደረሰባትን ግለሰብ በመግደሏ ለፍርድ ቀረበች

የፍርድ ሂደቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በፈረንሳይ ለበርካታ አመታት በእንጀራ አባትነት በኋላም በግዳጅ አግብቷት ባሏ ሆኖ ጥቃት ሲያደርስባት የነበረውን ግለሰብ ተኩሳ የገደለችው ሴት ለፍርድ ቀርባለች።

ቫለሪ ባኮት የተባለችው ይህች ሴት የእንጀራ አባቷ ሲደፍራት ገና የ12 አመት ልጅ ነበረች።

በወቅቱም ደፋሪው ግለሰብ ዳንኤል ፖሌቴ ታስሮ የነበረ ቢሆንም ከተፈታ በኋላ ወደዚያው ቤት ተመልሶ በጥቃቱ ቀጥሏል።

ታዳጊዋን አስገድዶ እንድታገባውም ካደረገ በኋላ አራት ልጆች አስወልዷታል።

ግፉ የበዛባት ቫለሪ በሽጉጥ የገደለችው በአውሮፓውያኑ 2016 መሆኑንም አምናለች።

በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንድትለቀቅ ፊርማ አሰባስበዋል።

ቫለሪ እንደምትለው በወሲብ ንግድ ካሰማራት በኋላ እንደገደለችው ተናግራለች።

ከገደለችውም በኋላ አስከሬኑን በሁለት ልጆቿ እርዳታ ብትደብቀውም በ2017 በቁጥጥር ስር ከመዋሏ ጋር ተያይዞ እንደገደለችው ተናዛለች።

የፍርድ ሂደቱ የበርካታ ፈረንሳውያንን ቀልብ የያዘ ሲሆን በርካቶችም በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን በተመለከተ መወያያም ሆኗል።

ይሄ ጉዳይ ጃኩሊን ሳቫጅ ከተባለች ሌላ ፈረንሳዊትም ጋር ተመሳሳይ ነው ተብሏል።

ግለሰቧ ለበርካታ አመታት ጥቃት ያደረሰባትን ባሏን መግዷሏን ተከትሎ ለፍርድ ቀርባ የነበረ ቢሆንም ፕሬዚዳንቱ ምህረት አድርገውላት በነፃ ተለቃለች።

የቫለሪ ጠበቃ እንዳሉት "ለ25 አመታት ያህል በአሰቃቂ ጥቃት ነው የኖረችው እናም ሴት ልጇም ቀጣይዋ ተጠቂ ትሆናለች የሚለው ፍራቻ እንድትገድለው ምክንያት ሆኗል" ብለዋል።

በባለፈው ወር የህይወት ታሪኳን የፃፈችው ቫለሪ ሁልጊዜም ቢሆን በከፍተኛ ፍራቻ ውስጥ ትኖር እንደነበረና ይህም ማክተም እንዳለበት እንደተሰማት አስፍራለች።

መደፈሯ በ12 አመቷ የጀመረው ቫለሪ ግለሰቡ በ25 አመታት የሚበልጣትና የ37 አመት ጎልማሳ ነበር ብላለች።

በመጀመሪያ ወቅት በደፈራትም ጊዜ ሁለት አመት ተኩል ተፈርዶበት ከዚያም እስሩን ጨርሶ ከተፈታም በኋላ ጥቃቱ መቀጠሉን ተናግራለች።

በአስራ ሰባት አመቷን እንዳስረገዛትና አስገድዶም እንዳገባትም መፅሃፏ ላይ አስፍራለች።

በተጨማሪም አካላዊ ጥቃት ያደርስባት የነበረው ይህ ግለሰብ በወሲብ ንግድም አሰማርቷት ነበር።

በራሱ ሽጉጥ እንደገደለችው ያመነችው ቫለሪ ራሷንና ልጆቿን ለመጠበቅ እንዳደረገችው አስረድታለች።