ምርጫ 2013፡ ዛሬ ድምጽ የሚሰጥባቸው ቦታዎች መኖራቸው ተገለጸ

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ከረፋድ 5 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ የሚሰጥባቸው ቦታዎች መኖራቸውን አስታወቀ።

ቦርዱ ይህን ያለው ትናንት ምሽት 5፡30 ላይ በሰጠው መግለጫው ነው።

በመግለጫው ላይ የምርጫ ቦርድ አምስት አባላት መግለጫ ለመስጠት የተገኙ ሲሆን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱኳን ሚደቅሳ ምርጫ "ከሞላ ጎደል እጅግ ጥሩ ነበር" ብለዋል።

የድምጽ መስጫ ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት እንዲራዘም ስለመወሰኑ ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፤ የድምጽ መስጫ ሰዓት ማራዘም ሳያስፈልጋቸው የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓታቸውን ያካሄዱ ምርጫ ጣቢያዎች ትናንት ምሽት ድምጽ ቆጠራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ከምርጫ ጣቢያዎች ከፍተኛ ቁጥር አንጻር ሁሉም ሊባል በሚችል መጠን የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ ሲያሰጡ ውለው አጠናቅቀዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ከትግራይ፣ ሶማሊ እና ሐረሪ ክልሎች በስተቀር በትናንትናው ዕለት፣ ሰኔ 14 2013 ዓ.ም ማከናወኗ ይታወሳል።

በሶማሊ እና በሐረሪ ክልሎች ደግሞ ጳጉሜን 1 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ የምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል።

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ላልተወሰነ ጊዜ ምርጫ አይካሄድም።

ከ37 ሚሊዮን በላይ መራጮች በተመዘገቡበት እና 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፎካከሩበት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ትናንት ከምሽቱ 3፡00 መጠናቀቁን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ለህዝባቸው አስተላልፈዋል።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ከ40ሺህ በላይ የአገር ውስጥ እና ከ200 በላይ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ተሰማርተዋል።

የምርጫ ቦርድ አባላትም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን መጎብኘታቸውን የገለፁ ሲሆን፣ ምርጫው ሴቶች እና ወጣቶችን ያሳተፈ መሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ታዛቢዎቹ በቀጣይ ጥቂት ቀናት የቅደሚያ ሪፖርት ዋና ዋና ግኝት የሚሏቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምርጫና መራጮች

የጸጥታ ችግር

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ትናንት በተካሄደው ምርጫ ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ችግር አላጋጠመም ሲሉ ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ በተመሳሳእ ምርጫው በሰላም ተካሄዶ መጠናቀቁን በሰጠው መግለጫው ላይ አመልክቷል።

በአማራ ክልል በአንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ ያልታጠቁ ሰዎች እርስ በእርስ ግጭት ፈጥረው የምርጫው ሂደት የተቋረጠበት ሁኔታ እንደነበር ሰብሳቢዋ አስታውሰዋል።

በአማራ ክልል ጎንጂ ምርጫ ክልል ውስጥ በሚገኝ አንድ ምርጫ ጣቢያ ውስጥ የአካባቢው ባለስልጣናት ገብተው አልወጣም ማለታቸው ስጋት ፈጥሮ፣ አንድ የምርጫ ቦርድ ምርጫ አስፈጻሚ አካባቢውን ለቅቆ ሊወጣ ችሏል። ይህን ለሚመለከተው አሳውቀናል ሲሉም አክለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ምርጫ አስፈጻሚዎች ስጋት ገብቷቸው ምርጫ ጣቢያ ያልከፈቱባቸው ቦታዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።

አክለውም ምስራቅ ሐረርጌ ምርጫ ክልል ውስጥ ያልተከፈቱ ምርጫ ጣቢያዎች አሉ። ይህ የመጀመሪያ ሪፖርት ነው ጉዳዩን እንመለከተዋለን ሲሉም አብራርተዋል።

በምዕራብ ሸዋ ኖኖ ምርጫ ክልል ሁለት ጣቢያዎች ላይ የታጠቁ ሰዎች ሂደቱን ረብሸው የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱ ተቋርጦ እንደነበር የተናገሩት ወ/ት ብርቱካን "ከዚህ ውጪ ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ችግር የለም" ሲሉ አረጋግጠዋል።

የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት

በአዲስ አበባ የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ያስረዱት የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ይሁን እንጂ ይህ ችግር ማጋጠሙ እንደታወቀ በተወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ችግሩ መቀረፉ ተመልክቷል።

ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ሲዳማ ክልሎች የቁሳቁስ እጥረት ማጋጠሙን ወ/ት ብርቱካን ተናግረዋል።

ሲዳማ

የድምጽ መስጫ ወረቀቶች በባለ 100 ተደርጎ መታሸግ ሲኖርባቸው በባለ 50 ተደርገው በመታሸጋቸው እጥረት ማጋጠሙን ያስረዱት ሰብሳቢዋ፣ 19 የምርጫ ክልሎች ላይ የምርጫ ወረቀት ብዛት በ50 በመቶ አጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት በሲዳማ ክልል ሁሉም ምርጫ ክልሎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደት መቋረጡን አብራርተዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያስፈልገው ሰነድ ለ19 የምርጫ ክልሎች እንዲደርስ መደረጉንም አስረድተዋል።

ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ለማድረስ ግን ከመሰረተ ልማት እና ከርቀት አንጻር አስቸጋሪ ነበር ያሉት ሰብሳቢዋ፣ ቦርዱ 1162 የምርጫ አዋጁ በሚፈቅደው መሠረት ምርጫው እንዲቋረጥ አድርጎ ዛሬ ማክሰኞ፣ ከረፋዱ 5 ጀምሮ በሲዳማ የምርጫ ክልሎች በሙሉ ሂደቱ ይቀጥላል ብለዋል።

የምርጫ አዋጅ 1162 ምርጫ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ በሚቋረጥበት ጊዜ፣ ለጊዜው ምርጫው እንዲቋረጥ ተደርጎ ሁኔታዎች የሚስተካከሉበት ሰዓት ተወስዶ ሂደቱ መቀጠል እንደሚቻል ይደነግጋል።

ጋምቤላ

ጋምቤላ በአራት የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት አጋጥሞ ነበር። በእነዚህ ምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ በቁሳቁስ እጥረት ምርጫው ተቋርጦ እንደነበረ የቦርዱ ሰብሳቡ ወ/ት ብርቱካን ተናግረዋል።

የድምጽ አሰጣጡ በተቋረጠባቸው አራቱ የምርጫ ክልሎች ጉዳይ ቦርዱ የሚሰጠው ውሳኔ ግልጽ ይደረጋል ብለዋል። በጋምቤላ ያሉ ሌሎች ምርጫ ክልሎች ግን ድምጽ አሰጥተው ወደ ቆጠራ መግባታቸውን እና ውጤትን በሂደት እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።

ምርጫ 2013

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ

በሁለት የምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት በማጋጠሙ ምርጫ መቋረጡን የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ ቻርተር አውሮፕላን በመጠቀም ቁሳቁሶች ወደ ጋምቤላ መላካቸውን ተናግረው በጉዳዩ ላይ የሚወሰነው ውሳኔ ግልጽ ይደረጋል ብለዋል።

ሰብሳቢዋ በዚህ ረገድ ለተፈጠሩ ጉድለቶች ሕዝቡን ይቅርታ እንጠይቃለን ሲሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዛሬ ጀምሮ በየምርጫ ጣብያው ውጤት መግለጽ እንደሚጀመር አስረድቷል።

አክሎም ቆጠራ ያጠናቀቁ ጣብያዎች በሙሉ በምርጫው የተገኘውን ውጤት ከዛሬ ጀምሮ መግለጽ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

ምርጫ ክልሎች ቢበዛ አምስት ቀን ድረስ ውጤት ለማሳወቅ ጊዜ እንደሚፈጅባቸው የተናገረው ቦርዱ፣ ነገር ግን በጊዜያዊነት ከስር ከስር እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

ምርጫ ቦርድ በ አስር ቀን ውስጥ ውድድር በተደረገባቸው የምርጫ ክልሎች ቢያንስ በጊዜያዊነት ውጤቶችን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።