ምርጫ 2013፡ የምርጫ ቦርድ አፈጻጸም ተስፋ ሰጪ ነው- ሽመልስ አብዲሳ

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ አፈጻጸም ተስፋ ሰጪ ነው አሉ።

"ይህ ምርጫ በብዙ ፈተና ውስጥ የተካሄደ ምርጫ ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ ብልጽግናን ወክለው ዕጩ ሆነው በቀረቡበት ጊንጪ ከተማ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

ሽመልስ አብዲስ በሚወዳደሩበት ምርጫ ጣቢያ፣ ጊንጪ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የለም። ዕጩ ሆነው የቀረቡት አራቱም ተፎካካሪዎች የብልጽግና ዕጩዎች ናቸው።

ዛሬ ማለዳ ከአዲስ አበባ 90 ኪሎ ሜትር የምትርቀው ጊንጪ ከተማ ከፍተኛ የሆነ ፀጥታ ኃይል ጥበቃ የታየ ሲሆን ኢንተርኔትም በጣም አዝጋሚ ነበር።

በጊንጪ ከተማ ነዋሪ የሆነችው አልማዝ ጅዳ አቶ ሽመልስ ለሚወዳደርበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን ለመላው ክልል ጥሩ እየሰሩ መሆኑን ትናገራለች።

"የምርጫ ቦርድ ያሳው ገለልተኛነት፣ ቦርዱ እየወሰነ ያለው ውሳኔ፣ እንዲሁም ተግባራቱን እያከናወኑ የሚገኙበት ሁኔታ ተስፋ ሰጥቶናል" ሲሉ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ እያካሄደች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ጦርነት እየተካሄደ ሲሆን፣ በተለያዩ አገሪቱ ክልሎች የፀጥታና የደኅንነት ስጋት ተደቅኗል።

በኦሮሚያ የክልሉ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊት በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ውጊያ እያካሄዱ ይገኛሉ።

ነገር ግን ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሚያስተዳድሩት ክልል ሰላማዊ መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ወራት ወደ ተለያዩ የክልሉ ከተሞች መጓዛቸውን ገልጸዋል።

ምርጫና መራጮች

"ኦሮሚያ ሰላማዊ ናት። የደኅንነት ስጋት ያለው በፌስቡክና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ነው። ዛሬ ዜጎች በሰላም እየመረጡ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ድምጻቸውን ለመስጠት ከተመዘገቡት 37 ሚሊዮን መራጮች መካከል 15.4 ሚሊዮን ያህሉ የተመዘገቡት በኦሮሚያ ነው።

በኦሮሚያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል።

ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ጫና ያሳድርብናል ቢሉም መንግሥት ግን ክሱን አይቀበልም።

"በዚህ ምርጫ እንዲሳተፉ የተቻለውን ሁሉ አድርገናል። ውሳኔያቸው የሚጎዳው እነርሱን ብቻ ነው፥ ነገር ገን ከአምስት ዓመት በኋላ ሌላ እድል አላቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታስቦ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ወደዚህ ዓመት የተሸጋገረው ብሔራዊ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 8,209 ዕጩዎችን ያረቡ ሲሆን በግል ደግሞ 125 ዕጩዎች በምርጫው ይሳተፋሉ።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኤርትራና ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ለቅቀው እንዲወጡ እየሰሩ መሆኑን ገለፁ