ምርጫ 2013፡ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ውጤት መቼ ይታወቃል?

አንዲት መራጭ ድምጽ ስትሰጥ

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ እየተካሄደ ነው። በዚህ ምርጫ ላይ በክልሎችና በፌደራል ምክር ቤቶች ውስጥ ላሉ መቀመጫዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች ይፎካከራሉ።

ዛሬ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ማለዳ ላይ የጀመረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ቀን ሙሉ ሲካሄድ ውሎ፤ ሌላ ተጨማሪ መመሪያ ከምርጫ ቦርድ አስካልተሰጠ ድረስ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል።

የድምጽ መስጠት ሂደቱ እንዳበቃ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የሕዝብ ታዛቢዎች የዕጩ ታዛቢዎች በሚገኙበት የድምጽ ቆጠራው ይጀመራል።

በቅድሚያ ደምጽ በየምርጫ ጣቢያው ይቆጠራል። ነገር ግን በጸጥታ መደፍረስ ወይም ተመሳሳይ አስገዳጅ ምክንያት ሲከሰት የምርጫ ጣቢያው የምርጫ አስፈፃሚ ለምርጫ ክልሉ ጥያቄ አቅርቦ ሲፈቀድ ወይም የምርጫ ክልሉ የምርጫ አስፈፃሚ ሲወስን የድምጽ ቆጠራው በምርጫ ክልሉ ጽህፈት ቤት ይካሄዳል።

ድምጽ አሰጣጡ እንደተጠናቀቀ የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ የሚከተሉትን ተግባራት የድምፅ ቆጠራ ሳይጀመር በፊት ያከናውናል

  • ቆጠራ ለመጀመር የዕጩ ወኪሎች፣ ከሕዝብ የተመረጡ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት እና የምርጫ ታዛቢዎች እና ሌሎች ምርጫ አስፈጻሚዎች እንዲገኙ ያደርጋል፡፡
  • በቂ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ ብርሃን መኖሩን ያረጋግጣል
  • ለምርጫ ጣቢያው የደረሰውን የድምጽ መስጫ ወረቀት ብዛት ይመዘግባል
  • በዕለቱ ድምጽ የሰጡ መራጮችን ብዛት ይመዘግባል
  • የተበላሹና ሥራ ላይ ያልዋሉ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ብዛት ይመዘግባል
  • ድምጽ ቆጠራ ከመጀመሩ በፊት የድምጽ መስጫው ሳጥን እሽጉ ያልተከፈተ፣ ሳጥኑም ያልተቀደደ፣ ወይም ብልሽት ያልደረሰበት መሆኑን መጀመሪያ የጠቀስናቸው አካላት በተገኙበት አረጋግጦ ቃለ ጉባኤ ይይዛል
  • ቀጥሎም ሳጥኑ ተከፍቶ ድምጽ የተሰጠባቸው ወረቀቶች በሙሉ ይወጣሉ
  • የድምጽ መስጫ ሳጥኑም ባዶ መሆኑ ይረጋገጣል፡፡
  • በመቀጠልም ምርጫው የተካሄደው ለተለያዩ ምክር ቤቶች ከሆነ ቆጠራው ለየብቻ ይካሄዳል። ለምሳሌ ለፌደራል እና ለክልል ምክር ቤቶች የተደረገ ምርጫ ከሆነ የሁለቱም ምክር ቤቶች ድምጽ ለየብቻ በየተራ ይቆጠራል እንዲሁም ወረቀቶቹ ይለያሉ።
  • የአንዱ ምክር ቤት ተቆጥሮ እና ለእያንዳንዱ ዕጩ የተሰጠው የድምጽ ቁጥር ተመዝግቦ እንዳለቀ የሌላው ምክር ቤት ቆጠራ በተመሳሳይ ይካሄዳል
  • በቂ ብርሃን የሌለ እንደሆነ የዕጩ ወኪሎች፣ ከሕዝብ የተመረጡ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት እና የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ይህንኑ በመግለጽ ቃለጉባኤ ይፈራረማሉ፤ ድምፆቹም ሳይቆጠሩ በጥበቃ ስር ይቆያሉ
  • የተቋረጠ የድምጽ ቆጠራ ሂደት በሚቀጥለው ቀን እጅግ ቢዘገይ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል
  • ከተጠቀሱት ሰዎች አንዱ በሂደቱ ላይ ቅሬታ ያቀረበ እንደሆነ የምርጫ ጣቢያው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን መርምሮ ወዲያውኑ ወይም ቢዘገይ ከ12 ሰዓት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል
  • ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው የድምጽ ቆጠራው ሁኔታዎች እስኪጣሩ እንዲቋረጥ ወይም እንዲቆም እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ዳግም ቆጠራ እንዲካሄድ ሊወስን ይችላል
ድምጽ የሚሰጥ ሰው

በየፈርጁ የተደረገው ቆጠራ ሲጠናቀቅም የሚከተሉት ተግባራት ይከናወናሉ

  • በምርጫ ጣቢያው የተደረገው የቆጠራ ውጤት
  • ለጣቢያው የደረሰውን የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ብዛት
  • በጣቢያው የተመዘገቡና ድምጽ የሰጡ መራጮችን ብዛት
  • ጥቅም ላይ የዋሉ፣ ያልዋሉ፣ የተበላሹና ዋጋ አልባ የሆኑ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ብዛት
  • እያንዳንዱ ዕጩ ያገኘውን የድምጽ ብዛት ይለያል
  • ቆጠራው በተጠናቀቀ በአንድ ሰዓት ውስጥ በምርጫ ጣቢያው ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ወጥቶ ለሕዝብ በይፋ ይገለፃል

በምርጫ ጣቢያ ደረጃ የመጀመሪያው ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ በተለያዩ ደረጃዎች ውጤቱ ይፋ ይደረጋል

  • በምርጫ ክልሉ ቆጠራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ውጤቱ በአምስት ቀን ውስጥ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል
  • ቦርዱ በአጠቃላይ የምርጫ ውጤት ተጠናቆ እስኪደርሰው ድረስ ከየምርጫ ክልሉ የመጣለትን ውጤት በጊዜያዊነት በቦርዱ ጽህፈት ቤት ሊገልጽ ይችላል
  • ነገር ግን የምርጫው ይፋዊ ውጤት በ10 ቀናት ውስጥ ካልተገለጸ ቦርዱ ጊዜያዊ ውጤቱን ይፋ ማድረግ ይኖርበታል
  • ቦርዱ ከድምፅ መስጫ ቀን በኋላ ባሉ 10 ቀናት ውስጥ ቀጣዮቹን መረጃዎች ይፋ የማድረግ ግዴታ አለበት
  • የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር
  • ድምጽ የሰጡ መራጮች ቁጥር
  • ድምጽ የሰጡና ያልሰጡ የተመዘገቡ መራጮች መጠን በመቶኛ
  • የተመረጡ ዕጩዎች የስም ዝርዝርና የተመረጡበት የምርጫ ክልል
  • የአሸናፊ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የግል ተወዳዳሪዎች ስምና ለየምክር ቤቱ ያሸነፉትን መቀመጫ ብዛት
  • ጥቅም ላይ የዋለ፣ ያልዋለ፣ ከጥቅም ውጭ የሆነ የድምጽ መስጫ ወረቀት
  • እያንዳንዱ ዕጩ በየምርጫ ጣቢያው ያገኘው የድምጽ ውጤት እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል

ነገር ግን በምርጫ ክልል ደረጃ በተገለጹ ውጤቶች ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች ውጤት መግለጹን እንዲዘገይ የሚያደርግ ከሆነ ይፋዊ ውጤት የሚገለጽበት ጊዜ እስከ 20 ቀን ድረስ ሊዘገይ ይችላል።

ድምጽ የምትሰጥ ሴት
ምርጫ 2013