ምርጫ 2013፡ ቦርዱ የምርጫ ሳጥኖች በመከፈታቸው ምርጫ የማይካሄድባቸው ቦታዎች አሉ አለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምጽ መስጫ ወረቀት የያዙ ሳጥኖች ተከፍተው በመገኘታቸው ነገ በአምስት የምርጫ ክልሎች የድምጽ አሰጣጥ እንደማይኖር አስታወቀ።
ነገ የድምጽ አሰጣጥ የማይካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች ግንደበረት ምርጫ ክልል (ምዕራብ ሸዋ ኦሮሚያ)፣ ተሁለደሬ ምርጫ ክልል 1 እና 2 (ደቡብ ወሎ አማራ)፣ ነገሌ ጉጂ (ኦሮሚያ) እና ደንቢያ ምርጫ ክልል (አማራ) ናቸው።
በቦርዱ ውሳኔ መሠረት በእነዚህ አምስት የምርጫ ክልሎች ለክልል ምክር ቤትም ሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደር ዕጩ አይኖርም ማለት ነው።
"ሲሰራጩ የነበሩ ሰማያዊ ሳጥኖች ተከፍተው ተገኝተዋል። ሳጥኖቹ ተከፍተው በተገኙ ቦታዎች ምርጫው እንዳይከናወን ቦርዱ ወስኗል" ሲሉ የምርጫ ቦርድ ኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ዛሬ እሁድ ዕለታዊ መግለጫቸው ተናግረዋል።
ደንቢያ
ሦስት የደንቢያ ምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ሰማያዊ ሳጥኖችን ከፍተው የድምጽ መስጫ ቡክሌቶችን መመልከታቸውን የምርጫ ቦርድ ቃል አቀባእ ሶሊያና በዛሬው ዕለት ተናግረዋል። "በዚህም ጉዳይ ምርመራ እንዲደረግ ለፌደራል ፖሊስ አሳውቀናል" ብለዋል።
የምርጫ ቁሳቁሶችን የያዙ ሳጥኖችን መክፈት ጥብቅ ወንጀል ነው ያሉት ሶሊያና በደንቢያ ምርጫ ክልል ነገ የድምጽ አሰጣጥ እንደማይኖር አሳውቀዋል።
ተውለደሬ ምርጫ ክልል 1 እና 2
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙት ተሁለደሬ ምርጫ ክልል 1 እና 2 በተመሳሳይ ሰማያዊ ሳጥን ተከፍቶ በውስጡ ያሉ የዕጩዎች ዝርዝርን በመታየታቸው በስፍራዎቹ ምርጫ አይካሄድም።
ግንደበረት ምርጫ ክልል
ምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኘው ግንደበረት ምርጫ ክልል ሰኞ ምርጫ የማይካሄድበት አራተኛው ምርጫ ክልል መሆኑን ሶሊያና ተናግረዋል።
"በግንደበረት ነገ የድምጽ አሰጣጥ የማይካሄደው ሳጥን ተከፍቶ ተገኝቶ ሳይሆን በአካባቢው የምርጫ አስፈጻሚዎች እጥረት ነበረ። ወረዳው በራሱ አስፈጻሚዎችን አሰልጥኖ ምርጫውን ለማስፈጸም ሊያሰማራ ሲል ስለተገኘ ግንበረት ላይ ደምጽ አናሰጥም" ብለዋል።
ነገሌ ምርጫ ክልል
በነገሌ ዕጩ የነበረ አንድ የግል ተወዳዳሪ 'በምርጫው ተመዝግቤ እና ሰርተፊኬት ተሰጥቶኝ በድምጽ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች ዝርዝር ላይ አልታየሁም' የሚል ቅሬታ ማቅረቡን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ በነገሌ ምርጫ ክልል ነገ የድምጽ አሰጣጥ እንዳይኖር መወሰኑን ሶሊያና ተናግረዋል።
በደቡብ ክልል በሚገኘው ሲቄ ምርጫ ክልል ሲቄ 1 እና 2 ሰማያዊው ሳጥን ተሰንጥቆ መገኘቱን ሶሊያና ተናግረዋል። በሳጥኑ ውስጥ የነበሩት የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ባለመነካታቸው እንዲሁም ምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የሁሉም ዕጩዎች ወኪሎች እና የጸጥታ አካላት ባሉበት ቃለ ጉባኤ ተይዞ ሳጥኑ እንዲለወጥ በመደረጉ ምርጫው እንዲከናወን መደረጉን ገልጸዋል። ስለዚህ ሲቄ ምርጫ ክልል 1 እና 2 ነገ የድምጽ አሰጣጥ ይከናወናል።
ነገ በሚካሄደው ምርጫ ምን ያህል ሕዝብ ድምጽ ወጥቶ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሶሊያና ሲመልሱ፤ "ይህ ነው የተባለ ግምት የለም ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበረ ምርጫ ከተመዘገበው ሕዝብ 80 በመቶ የሚሆነው ድምጹን ሲሰጥ ነበር ብለዋል።"
ለስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ በሁለት ዙር ድምጽ እንዲሰጥ በተወሰነው መሰረት በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ሰኔ 14/2013 ዓ.ም መራጮች ድምጽ ይሰጣሉ።
ሁለተኛው ዙር የምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ከሁለት ወር በኋላ ጳጉሜ 01/2013 ዓ.ም በሁለት ክልሎችና በቀሩት ስፍራዎች ውስጥ ይከናወናል።












