ምርጫ 2013፡ የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት በደቡብ ክልል

ሐዋሳ
የምስሉ መግለጫ, ሐዋሳ

በደቡብ ክልል በሚቀጥለው ሰኞ በሚካሄደው ምርጫ፣ 23 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ የክልሉ የምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍሬው በቀለ ለቢቢሲ ገለፁ።

እነዚህ ፓርቲዎች ከ1700 በላይ ዕጩዎችን አስመዝግበዋል።

በአጠቃላይ በደቡብ ክልል 8ሺህ 109 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ኃላፊው ነግረውናል። ነገር ግን በሁሉም ጣቢያዎች ድምፅ መስጠት አይቻልም።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ከጥቂት ጊዜያት በፊት እንዳስታወቀው፤ አቶ ፍሬው በቀለ እንዳስረገጡትም የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ያለአግባብ ምዝገባ በማድረጋቸው እንዲሁም በፀጥታ ምክንያት ድምፅ አይሰጥባቸውም።

ኃላፊው ጨምረው በሲዳማ ክልል ባሉ 19 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫው ይካሄዳል፤ የሲዳማ ክልል ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ሰኞ ዕለት ክፍት ናቸው ይላሉ።

አቶ ፍሬው አክለው በደቡብ ክልል ከ6 ሚሊየን በላይ ሕዝብ በሲዳማ ክልል ደግሞ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰው ድምፁን ላሻው ዕጩ ለመስጠት እንደተመዘገበ ይናገራሉ።

ኃላፊው መራጮች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ርቀታቸውን ጠብቀው እንደሚመርጡ ይናገራሉ። ይህን ለማድረግ ያስችለን ዘንድ ከጤና ቢሮዎች ጋር እየሠራንም ነው ይላሉ።

መራጩ የኮቪድ-19 ጥንቃቄ እንዳይለየው በማለት ሕግጋቱን የሚያስከብሩ የምርጫ አስተባባሪዎች በየቦታው ተሰመርተዋል ሲሉ ያክላሉ።

አቶ ፍሬው ምናልባት በቀጣዩ ሰኞ ሊያሰጋ የሚችለው ጉዳይ ዝናብ ነው ይላሉ። ምርጫ በተፈጥራዊ አሊያም በሰው ሰራሽ ምክንያት መካሄድ ባይችል ምን ልታደርጉ አሰባችሁ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊው ይህ በምርጫ ቦርድ መመሪያ መሠረት የሚከናወን ነው ሲሉ ይመልሳሉ።

ምርጫው በተለያዩ ምክንያቶች መካሄድ ባይችል የማዘግየት ወይም የማራዘም ሥልጣን ያለው ብሔራዊው ቦርድ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ምርጫው ሰኞ 12 ሰዓት ጀምሮ ምሽት 12 ሰዓት እንደሚጠናቀቅ የሚያወሱት ኃላፊው በጣቢያዎች ውጤት መግለፅ የሚጀመረው በነጋታው ከጠዋት ጀምሮ ነው ይላሉ።

የምርጫ ክልሎች ውጤት ገለፃ ፍጥነት የሚወሰነው እንደ ምርጫ ክልሉ ስፋት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ፍሬው አጠቃላይ ውጤቱን የመግለፅ ኃላፊነት ግን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው ይላሉ።