ምርጫ 2013፡ ኢዜማ ምርጫው ከመጠቃለሉ በፊት መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ጉዳይ አመለከተ

የኢዜማ መሪ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ዛሬ እየተከናወነ በሚገኘው ምርጫ ላይ አስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን እና በምርጫው ላይ ታይተዋል ያላቸውን ችግሮች ዘርዝሯል።

በዛሬው መግለጫ የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ምርጫው ከመጠቃለሉ በፊት አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጓቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በአማራ እና ደቡብ ክልል በተለያዩ ምርጫ ክልል የኢዜማ ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ ተከልክለዋል ብለዋል። እንዲገቡ የተደረጉ ታዛቢዎችም ከገቡ በኋላም እንዲወጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ጉዳዩን ለመንግሥት አካላት እና ለምርጫ ቦርድ ስናሳወቅ ቆይተናል ያሉት የፓርቲው መሪ ይህ ግን አጠቃላይ የምርጫው ግምገማ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"ይህ የምርጫው ድምዳሜ ነው ማለት አይደለም። ችግሩ የተፈጠረበትን ትክክለኛውን ሁኔታ ለማወቅ እየሥራን ነው" ብለዋል።

"በአንድ ቦታዎች ድምጽ መስጠት ተጠናቋል ብለው ቆጠራ ጀምረው ታዛቢዎቻችንን እንዲባረሩ አድርገዋል። በአዲስ አበባ ደግሞ ምርጫ ጣቢያዎች ሳይከፈቱ መዘግየት ነበሩ። በአንዳንድ ቦታዎች መፍትሄ ያገኙ ያሉ አሉ። ይሁን እንጂ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ምርጫውን አዘግይቶታል። መራጮች ለሁለት እና ሦስት ሰዓት ቆመዋል" ብለዋል።

ቀደም ሲል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫው ሂደትን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ከአማራ ክልል በርካታ ቅሬታዎች ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል እንደደረሷቸው ተናግረው ነበር።

"ድብደባዎች እና ባጅ መንጠቅ የመሳሳሉ እጅግ አሳሳቢ ሪፖርቶች ደርሰውናል" ብለዋል ነበር ሰብሳቢዋ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በሰልፍ ላይ የሚገኙ መራጮች ሳይሰላቹ ጠብቀው ድምጻቸውን እንዲሰጡ ከመምከራቸው በተጨማሪ ምርጫ ቦርድም ዘግይተው በተከፈቱ ቦታዎች የድምጽ መስጫ ሰዓቱ እንዲራዘም ጠይቀዋል።

ኢዜማ በጋዜጣዊ መግለጫው አዲስ አበባን ሳይጨምር ያጋጠሙ 207 ክስተቶችን ሪፖርት እንደተደረጉለት ተናግረዋል።

ምርጫ 2013

አጋጠሙ ከተባሉ ከስተቶች ምንድን ናቸው?

ጋሞ ዞን ቁጫ ወረዳ ሐሰተኛ የድምጽ መስጫ ወረቀት ይዘው የተገኙ ግለሰቦች ሰላም በር ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ ብለዋል የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ።

"ካድሬዎች አስተባባሪ ነን እያሉ ሰልፍ ውስጥ እየገቡ ቅስቀሳ ለማድረግ ሞክረዋል" ያሉት ብርሃኑ ነጋ፣ ታዛቢዎችን ማስወጣት፣ የኮሮጆ መሰበር የገጠመበት ቦታ እንዳለ አስታውቀዋል።

ከንጋት 12 ሰዓት በፊት ምርጫ ማካሄድ ተጀምሮ ነበርም ሲሉም ተናግረዋል።

ምሥራቅ ጎጃም የአካባቢው ባለስልጣናት የምስጢር ድምጽ መስጫ ቦታ እየገቡ ድምጽ እያሰጡ ነበር ያሉት የኢዜማ መሪ፣ ሚሊሻዎች ታጥቀው ምርጫ ሲያስፈጽሙ ነበር ሲሉ አክለዋል።

ጋምቤላ እና ሰሜን ሸዋ ላይ ምርጫ ተጠናቋል ብለው ቆጠራ እየተካሄደባቸው ያሉባቸው ቦታዎች መኖራቸውንም ተናግረዋው፣ በአዳማ እና አሶሳ ተመዝግበው ድምጽ ያልሰጡ ሰዎች እያሉ ምርጫው ተጠናቋል ተብሎ በአሁኑ ሰዓት ቆጠራ እየተካሄደ ነው ሲሉ አክለዋል።

ኢዜማ ከአንድ ሺህ በላይ ዕጩዎችን በመላው አገሪቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት ዕጩ አድርጎ አቅርቧል።

ምርጫና መራጮች