ምርጫ 2013፡ በኢትዮጵያ ምርጫ ዙሪያ በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ ሰኞ ለሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ እየተዘጋጀች ባለችበት ወቅት አንዳንዶች የተሳሳቱ መረጃዎችን በይነ መረብ ላይ እያሰራጩ ነው።
ከተቀረው የአፍሪካ ክፍል አንጻር በኢትዮጵያ ያለው የማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ተደራሽነት ዝቅተኛ ቢሆንም እንደ ብሔራዊ ምርጫ ባሉ ክስተቶች ዙሪያ ተጠቀዋሚነቱ በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።
ለብሔራዊ ምርጫው ድምጽ ከመሰጠቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ባለፈው ሳምንት ፌስቡክ የተሳሳቱ መረጃዎች ሲለጥፉ የነበሩ ያላቸውን አካውንቶችና ገጾችን ዘግቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከማስረከብ 'ሞትን እመርጣለሁ' አላሉም
በምርጫ ዘመቻወ ወቅት በስፋት ከተጋሩ ጉዳዮች አንዱ በሐሰት የተዘጋጀው እና ከገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ስብሰባ በድብቅ ወጥቷል የተባለው የድምጽ ቅጂ ነው። ይህ በድብቅ የተቀረጸ የተባለው ድምጽ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ድምጽ ይዟል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከመልቀቅ "መሞትን እመርጣለሁ" ሲሉ ይሰማሉ።
ድምጹ መጀመሪያ የተሰራጨው መቀመጫውን በአሜሪካ ባደረገው ኬሎ ሚዲያ በተባለው የበይነ መረብ የዜና አገልግሎት ሲሆን ድምጹም ትክክለኛ መሆኑን ጠቅሷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጽህፈት ቤት ድምጹ ሐሰተኛ መሆኑን በመግለጽ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጧቸውን የተለያዩ የማይዛመዱ አስተያየቶችን አንድ ላይ አሰባስቧል" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ቢቢሲ አማርኛ ድምጹን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ድምጹ ተቆራርጠው የተገጣጠሙ እንዲሁም የድምጽ መጠኑ እና የድምጽ ጥራቱ ልዩነቶች የተስተዋሉበት ሲሆን በዚህም የተቀነባበረ መሆኑን ይጠቁማል።
ሦስት የተለያዩ የድምጹ ክፍሎች ቀደም ሲል ተቀርጸው ለሕዝብ ከቀረቡ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ንግግሮች የተገኙ መሆናቸውም ተለይቷል።
ኢትዮጵያ በግብጽ ላይ የኒውክሌር ጥቃትን አላቀደችም
ይህ በጣም የማይመስል ቢሆንም የሕዳሴው ግድብ ግንባታን ተከትሎ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ያለውን አለመግባባት ያሳያል።
ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሚኮሩባቸው ስኬቶች መካከል አንዱ ቢሆንም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ያለው የውሃ ፍሰት የመቀነስ ስጋት የውዝግብ መነሻ ሆኗል።

መቀመጫውን ግብጽ ያደረገ የፌስቡክ ገጽ ኢትዮጵያ በግብጽ ላይ የኒውክሌር ጥቃት ለመሰንዘር አቅዳለች የሚለውን ጨምሮ ስለ አለመግባባቱ ያልተረጋገጡ ጉዳዮችን እየለጠፈ ነው።
"የሕዳሴ ግድብ ቀውስ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን በጦዘበት ወቅት በግብጽ ላይ የኒውክሌር ጥቃት ለማድረስ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን በደርዘን የሚቆጠሩ ዜናዎች [መረጃዎች] መኖራቸው በጣም ይገርማል" ይላል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የላትም። በአሁኑ ጊዜ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ያለው አንድም የአፍሪካ አገርም የለም።
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት የተባበሩት መንግሥታት ከኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነጻ ዞን አካል ሲሆኑ የኒውክሌር መሣሪያ እንደማይኖራቸው ቃል ገብተው ተገዢነታቸውም እንዲጣራ ተስማምተዋል።
የመራጮች ምዝገባ ቁጥሮች ተጋኗል?
በበርካታ ክልሎች በተዋቀረች አገር ውስጥ በየአካባቢው የተመዘገቡት የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ አለመግባባት የሚያስነሳ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን ይፋዊ የምዝገባ ቁጥሮች ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ተከታታይ የማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ተጋርተዋል።
በምርጫ ቦርድ የተሰጠው አሃዝ የመራጮችን ብዛት በትክክል የሚያንፀባርቅ መሆኑን ማረጋገጥ ባንችልም [የሕዝብ ቆጠራ ለመጨረሻ ጊዜ በኢትዮጵያ የተካሄደው በ1999 ዓ.ም ነበር] እየተጋሩ ያሉት መረጃዎች የማጭበርበር ጥያቄያቸውን የሚደግፉ ምንም ማስረጃዎችን አይሰጡም።
ገዢውን ፓርቲ ይደግፋሉ ተብሎ በሚጠበቁ የተወሰኑ ብሔሮች ዘንድ ሆን ተብሎ ቁጥሩ እንዲጋነን ተደርጓል በሚል አንዳንዶች ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኝ አንድ የተቃዋሚ ደጋፊ "የዚህ ምርጫ ሁሉም ገጽታ የተበላሸ ነው" ቢልም ምንም አይነት ማስረጃ ግን አላቀረበም።
ይህ ልጥፍ የሚያመለክተው መረጃ በግንቦት መጀመሪያ ላይ የተለቀቁ ቁጥሮችን ነው። ምርጫ ቦርድ በአንዳንድ አካባቢዎች የምዝገባ ችግሮች እንደነበሩ ካረጋገጠ በኋላ ቁጥሩ ላይ ክለሳ ተደርጓል።
ይህ ግን ሰዎች ጊዜ ያለፈባቸው አሃዞችን በመጠቀም ጥያቄ እያነሱ እንደገና መረጃውን ከማስተላለፍ አላገዳቸውም።
የሕዝብ ቆጠራ በ2009 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በተደጋጋሚ ተላልፏል። መጀመሪያ በደኅንነት ጉዳዮች አሁን በቅርቡ ደግሞ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በሌላ ጊዜ እንደከናወን ተወስኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግሥታት ተሽከርካሪ የምርጫ ዘመቻ አድርገዋል?
በተባበሩት መንግሥታት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ጥንቃቄ የተሞላበት ነው።
አንዳንድ ተቃዋሚ ድርጅቶች በትግራይ ክልል በተፈጠረው ግጭት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለልተኛነት ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ድርጅቱ የተከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በበቂ ሁኔታ አልያዘም ሲሉ ይከሳሉ።
ተቃዋሚዎች በተለይም በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት አስተባባሪ የሆኑት ካትሪን ሶዚ በሰጡት ቃለ ምልልስ በትግራይ የተከሰተውን ግጭት "የሕግ ማስከበር ተግባር" ነው ማለታቸውን ይጠቅሳሉ።

ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰማያዊ ቀለም ያለውን የተባበሩት መንግሥታት የተሽከርካሪ ሰሌዳ ባለበት መኪና የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የሚያሳየው ፎቶግራፍ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተሰራጭቷል።
ምስሉ የተወሰደው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኦሮሚያ ክልል የምርጫ ዘመቻ ባደረጉበት ወቅት ነው። ባለሰማያዊው የተባበሩት መንግስታት የተሽከርካሪ ሰሌዳ ያለባቸው ምስሎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የትዊተር ገጽ ላይም ይገኛሉ።
ምስሎቹ እውነተኛ ቢመስሉም መኪናው በተባበሩት መንግሥታት የተሰጠ መሆኑን ወይም ለምን የተባበሩት መንግሥታት ሰሌዳን አንደተጠቀመ አይታወቅም።
ጥያቄ በሚፈጥር ሁኔታ በዚያው ቀን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶግራፍ አንሺ በለጠፈ አንድ ፎቶ ላይ ይኸው ተመሳሳይ ተሽከርካሪ ሰሌዳው [ታርጋው] ተነስቶ ይታያል።
የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የተባበሩት መንግሥታት በፌዴራል እና በክልል ደረጃ ለሚገኙ የመንግሥት ሚኒስትሮች መኪና መለገሱ የተለመደ ተግባር ነው" ብለዋል።
አክለውም እነዚህ ተሽከርካሪዎች የተባበሩት መንግሥታት ንብረት ባይሆኑም አንዳንድ ጊዜ ከግብር ጋር በተያያዘ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሌዳ ይኖራቸዋል ብለዋል።
"ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ በሚመለከት ምን እንደተፈጠረ እያጣራን ነው" ብለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ለማግኘት ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ብናቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘንም።















