የተባበሩት መንግሥታት በኮሮናቫይረስ ወቅት ከዓለም ሕዝብ አንድ በመቶው ተፈናቅሏል አለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኮሮናቫይረስ ባለበት በዚህ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ሰዎች ቁጥር 82 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።
ይህ ቁጥር በአስር ዓመታት ውስጥ በእጥፍ የጨመረ ሲሆን ከ1 በመቶ በላይ የዓለም ሕዝብ ተፈናቅሏል እንደማለት ነው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለአገራት የሚቀርብ የጥገኝነት ጥያቄንና አጠቃላይ ፍልሰትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ምክንያት ይሆናል ተብሎ እንደነበር ድርጅቱ ገልጿል።
ሆኖም ባለፈው ዓመት 11.2 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ይህ ቁጥር እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ከተፈናቀሉ ሰዎች የበለጠ ነው።
ግጭት፣ አመፅ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮችን ለስደት የዳረጉ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል።
ከዚህ ውስጥ እጅግ የበዙት በአገራቸው ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆኑ አገራት የጣሏቸው የጉዞ እገዳዎች ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ማቋረጥ እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው የተመልክቷል።
በሌላ በኩል ከተፈናቃዮች መካከል ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ የቻሉት 250 ሺህ ስደተኞች ብቻ ሲሆኑ በተሰደዱበት አገር ውስጥ ኑሮ እንዲመሰርቱ የተደረጉት 34 ሺህ ብቻ መሆናቸውን የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።
የኤጀንሲው ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ "በቀዳሚነት ሰዎች እንዲሰደዱ የሚያስገድዱ ግጭቶችን እና ችግሮችን ለመፍታት እጅግ የላቀ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልገናል" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት የኮሮናቫይረስ ገደቦች መላላታቸውን ተከትሎ በተያዘው ዓመት ግጭቶች ሊበራከቱ ይችላሉ ብሎ እንደሚሚሰጋ ገልጿል።
ረዘም ላለ ጊዜ በሚቆይ ግጭት፣ በከባድ የአየር ሁኔታ እና በወረርሽኙ ምክንያት የከፋ የምግብ እጥረትን ሊከሰትና የምግብ ቀውስ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችልም አስጠንቅቋል።
ደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ሶሪያ የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋልም ሲል ኤጀንሲው ገልጿል።
በሌላ በኩል ኮሮናቫይረስ በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ119 ሚሊዮን እስከ 124 ሚሊዮን እንዲደርስ ምክንያት ይሆናል የሚል ግምት ተቀምጦ ነበር።
ከጠቅላላው ተፈናቃዮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወይም 48 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት በአገራቸው ውስጥ ተፈናቅለው የሚገኙ ስለመሆናቸውም ድርጅቱ ገልጿል።
በወረርሽኙ ምክንያት ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ማቋረጥ ከባድ ቢሆንም አንዳንድ አገራት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ግዛታቸው እንዲገቡ እየፈቀዱ ነው ብሏል።
ኡጋንዳ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ባለው ውጊያ ምክንያት ወደ ግዟቷ ለሚሸሹ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ በማዘጋጀት ጭምር እየተቀበለች መሆኑ ተጠቁሟል።
ከአገራቸው ውጭ ከሚሰደዱት መካከል ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት ከአምስት አገሮች የመጡ ናቸው።
አሁን 10 ዓመት የሞላው የሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት 13.5 ሚሊዮን ሰዎችን አፈናቅሏል።
ይህም ከግማሽ በላይ የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር የሚሸፍን ነው። ከተፈናቀሉት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከአገራቸው ውጪ የተሰደዱ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ሆነዋል።
ከዚህ ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ተፈናቃዮች በጎረቤት አገራት ተጠልለው ይገኛሉ።
በተመሳሳይ ከስደተኞች የሚወለዱ ህፃናት ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል። እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት ከስደተኞች መወለዳቸውን የስደተኞች ድርጅቱ አመልክቷል።
ጉዳዩ በጥቅሉ ሲታይ አስጊ ቢሆንም አሜሪካ እንደ አውሮፓውያኑ በ2021፤ 62 ሺህ 500 እና በ2022 ደግሞ 125ሺህ ስደተኞችን ለመቀበል ቃል ገብታለች ተብሏል።
እንዲሁም ኮሎምቢያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ቬኔዝዌላውያንን በጊዜያዊነት ለማስጠጋት መወሰኗን ተስፋ ሰጪ ምልከቶች ናቸው ሲል የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት ገልጿል።












