የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አዲስ ጳጳስ ሾመች

አዲሱ ጳጳስ ሲሾሙ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብጹዕ አቡነ ቄርሎስን አምስተኛው ፓትሪያርክ አድርጋ መቀባቷን የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ትናንት እሁድ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

በአሥመራ ከተማ ውስጥ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች መገኘታቸውን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

አንዳንዶች ግን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀደሞ የተሰየሙ ፓትሪያርክ በህይወት አስካሉ ድረስ አዲስ ጳጳስ መሾም እንደማትፈቅድ በመጥቀስ ትችት ሰንዝረዋል።

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሦስተኛው ፓትሪያርክ አቡነ እንጦኒዮስ አስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ቤተክርስቲያኒቱን ሲመሩ የቆዩ ሲሆን ከሐይማኖቱ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት ያራምዳሉ ተብለው ሲከሰሱ ነበር።

አቡነ እንጦኒዮስ ለረጅም ጊዜ የአገሪቱ መንግሥትን ሲተቹ የቆዩ ሲሆን፤ በዚህም ለ15 ዓመታት ከመንበራቸው ተነስተው በቁም አስር ላይ መቆየታቸው ይነገራል።

ከሁለት ዓመት በፊት የኤርትራ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ፓትሪያርኩን አውግዘው ከመንበራቸው በማንሳት የእምነቱ ተከታዮች "እውቅና እንዳይሰቷቸውና ስማቸውንም እንዳያነሱ" አዘው ነበር።

ፓትሪያርኩ ከቤተክርስቲያኗ አባልነት የተገለሉ ቢሆኑ በቤተክርስቲያኗ ባለቤትነት ስር በሆነ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸዋል።

የአዲሱን ጳጳስ ሹመት በተመለከተ የወጣው መግለጫ ላይ አሁን የፓትሪያርክነት ሹመቱ የተከናወነው "በቤተክርስቲያኗና በቅዱስ ሲኖዶሱ ሕግና ሥርዓት መሠረት" መሆኑን አመልክቷል።

ብጹዕ አቡነ ቄርሎስን

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

የምስሉ መግለጫ, ብጹዕ አቡነ ቄርሎስን

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአገሪቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመላው ኤርትራ በእጇ የነበሩ ትምህርት ቤቶችን መንግሥት መውረስ መቀጠሉን ገልጻለች።

የኤርትራ መንግሥት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ንብረት የሆኑ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችን በ2012 ዓ.ም እንደወረሰ ቤተክርስቲያኗ ማሳወቋ ይታወሳል።

የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት ለኤርትራ ትምህርት ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ የተወሰደውን እርምጃ መረዳት እንዳልቻሉና ግራ እንደተጋቡ ገልጸዋል። ጨምረውም የቤተክርስቲያኒቱን ንብረት የመውረሱ እርምጃ ትክክለኛ ዓላማ ምን እንደሆነ እንዳልገባቸው አመልክተዋል።

ቤተክርስቲያኗ በጻፈችው ይፋዊ ደብዳቤ ላይ "በኃይል የተወሰዱብን ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚውሉ ተቋሞቻችን እንዲመለሱልንና ሁሉንም አገልግሎታቸውን መልሰው እንዲያከናውኑ መጠየቃችንን ፈጽሞ አናቆምም" ብላለች።

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መንግሥት ንብረቶቿን መውረሱና ትምህርት ቤቶችን መዝጋቱን አውግዛዋለች።

ሐይማኖት በኤርትራ

ኤርትራ ውስጥ የኦርቶዶክስ ክስትና እምነት ዋነኛ ከሚባሉት ሐይማኖቶች መካከል አንዷ ናት። በአገሪቱ ውስጥ በሕጋዊነት እንዲንቀሳቀሱ ተፈቀደላቸው የእምንት ተቋማት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የሉተራን ቤተክርስቲያንና የሱኒ አስልምና ናቸው።

ኤርትራ የእምንት ነጻነትን በመገደብ በኩል በተደጋጋሚ ስትወቀስ የቆየች ሲሆን በዚህም በርካቶች ለእስር መዳረጋቸው ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል።

ነገር ግን በቅርቡ የኤርትራ መንግሥት ከሚያራምዱት እምንት ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የነበሩ ሰዎችን መፍታቱ ተነግሯል።

የኤርትራ መንግሥት የጴንጤኮስታል እና የኢቫንጀሊካን እምነቶች የውጭ መንግሥታት መጠቀሚያ ናቸው በሚል ይከሳል።

በዚህ ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የሐይማኖት ነጻነት ኮሚሽን ኤርትራ በእምንት ነጻነት ላይ በምታደርሰው ጭቆና ምክንያት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በተለየ ሁኔታ እንዲመለከታት ጠይቆ ነበር።

ከ30 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ነጻ ከወጣች በኋላ ኤርትራ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የምትመራ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባት ወታደራዊ አገር ሆና ቆይታለች።

ምርጫ አድርጋ የማታውቀው ኤርትራ አገራዊ ምክር ቤት የሌላት ሲሆን ረቂቅ ሕገ መንግሥት አዘጋጅታ ሳይጸድቅና በሥራ ላይ ሳይውል አስካሁን እንደቆየ ይነገራል።