የሞናሊዛ ቅጅ ከ 300 ሺህ ዶላር በላይ ሊሸጥ እንደሚችል ተገመተ

የሞናሊዛ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, © Christie's Images Ltd, 2021

የዝነኛው የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ የሞናሊዛ ሥዕል ቅጅ በፓሪስ በጨረታ ሊሸጥ ሲሆን እስከ 365 ሺህ 645 ዶላር ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡በ 17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በዳ ቪንቺ ተከታይ የተሳለ ሲሆን የቀድሞ የስዕሉን ባለቤት ሬይመንድ ሄኪንግ ተከትሎ ሞናሊዛ ሄኪንግ በመባልም ይታወቃል፡፡እአአ በ 1977 ህይወቱ ያለፈው ሄኪንግ በሉቭር ሙዝየም የሚገኘውን ድንቅ ሥራ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ አንስቶ ነበር፡፡የጥንቱ ቅጅ ፓሪስ በሚገኘው ክሪስቲ የጨረታ ቤት ለሽያጭ ይቀርባል፡፡ሄኪንግ ስዕሉን በ 1950 ዎቹ ኒስ ከሚገኘው የኪነጥበብ ነጋዴ ነበር የገዛው፡፡

"ሥራው እና ታሪኩ ሞናሊዛ እና የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ሁል ጊዜ የያዝዋቸውን አስገራሚ ውበቶች ያሳያሉ" ክሪስቲ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።የኦልድ ማስተር ፔይንቲንግስ ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር የሆኑት ፒየር ኤቴንን ጠቅሶም ሞናሊዛ ሄኪንግ "ለሥነ-ጥበባት ፍቅር ህልም ያለው ሰው ውጤት ነው። ሬይሞንድ ሄኪንግ የስነ ጥበብ ተቆርቋሪና በታሪክ አዋቂዎችም ዘንድ ስሙ የሚጠቀስ ነው" ብለዋል፡፡የመጀመሪያው ሞናሊዛ ስዕል ምናልባትም በዓለም ላይ በጣም ዝነኛ ስዕል እንደሆነ የሚታመን ሲሆን ጣሊያናዊው ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ደግሞ ከዓለማችን ታላላቅ አርቲስቶች አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ዋና ሥራው በ 16 ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደተሳለ ይታመናል፡፡የሞናሊዛ ስዕል እአአ በ 1911 ሉቭር መሰረቁን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡

በዓለም ላይ በጣም ከሚጎበኙ ሙዝየሞች ተቀጣሪ የነበሩት ቪንቼንዞ ፐሩጊያ ሌሊቱን ሙሉ በኩሽና ውስጥ ተደብቆ በመቆየት የ ዳ ቪንቺን ስዕል ሰርቋል፡፡በ 1913 በፍሎረንስ ለሚገኝ ለጥንታዊ ቅርሶች ነጋዴ ሊሸጥ ሲሞክር ተይዞ ተመልሷል፡፡በ 1960 ዎቹ በለንደን አፓርታማ ውስጥ የተገኘው "ቀደምት ሞናሊዛ" በመባል የሚታወቀውን የስዕል ባለቤትነት አስመልክቶ ከሁለት ዓመት በፊት የመረረ ጥያቄ ተቀስቅሶ ነበር ፡፡