ከ20 ሺህ ብር በላይ የሚወጣበት የኢትዮጵያ ዘመናዊ የንቅሳት ገበያ

የፎቶው ባለመብት, Hena tattoo
ሰውነታቸው ላይ ንቅሳት ለማሳረፍ ወደ ንቅሳት ቤቶች ጎራ ከሚሉ ሰዎች መካከል በፍቅር ወይም በትዳር የተጣመሩ ጥንዶች ይገኙበታል።
"ጥንዶቹ ፍቅራቸውን ለመግለጽ ሴቷ የወንዱን፣ ወንዱ ደግሞ የሴቷን ስም አሊያም የስም መጀመሪያ ፊደላትን መነቀስ የተለመደ ሆኗል" ይላል የንቅሳት ባለሙያው (ታቱ አርቲስት) ሔኖክ ጥላሁን።
ሆኖም በጥንዶቹ መካከል ንፋስ ገብቶ መራራቅ ሲመጣ "ለየብቻ ይመጡና ንቅሳቱን ቀይርልኝ" ብለው እንደሚጠይቁት ይናገራል።
ይህንን በመሰሉ አጋጣሚዎች የተሞላውን የንቅሳት ሥራ፤ ሰዎች ሐሳባቸውን ለማንጸባረቅ ያውሉታል።
ዮሴፍ ተስፍዬ ይባላል። 28 ሺህ ብር አውጥቶ በሁለቱም እጆቹ ከትከሻው እስከ መዳፉ አንጓ 'የውስጤን ሐሳብ ይገልጹልኛል' ያላቸውን የተለያዩ ምስሎችና ጽሁፎች ተነቅሷል።
ለእሱ የደስታ ምንጭ የሆነው ንቅሳቱ በተመልካቾች ዘንድ ሁለት ዓይነት አስተያየት ይቀርብበታል። አንዱ "ምን ነካህ?" ሲሆን ሌላኛው ደግሞ "ያምራል" የሚል ነው ይላል።
ነገር ግን በሚሠራበት አካባቢ ንቅሳቱ እንዳይታይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርግም ይናገራል።
ሳምራዊት ተስፋዬ እና ኤልኤዘር ሙሴም በተመሳሳይ መነሻ የተለያዩ የሰውነት ክፍላቸውን ተነቅሰዋል።
ለመሆኑ በአዲስ አበባ ምን አይነት ንቅሳቶች ይዘወተራሉ? ምን ያህል ገንዘብስ ይወጣባቸዋል?
የንቅሳቶች ይዘት እና ምክንያት
የንቅሳት ባለሙያው ሔኖክ ጥላሁን ቀደም ሲል ሥዕሎችን ይስል እንደነበር ይናገራል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ ንቅሳትም አንድ የጥበብ ዘርፍ በመሆኑ 'ሄና ታቱ' የሚል ድርጅት በመክፈት ንቅሳትን መተዳዳሪያው ካደረገ ከስምንት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል።
ንቅሳት የሚፈልጉ ሰዎች ከተዘጋጀ የንቅሳት ዝርዝር ውስጥ መርጠው ወይም የፈለጉትን ማንኛውንም አይነት ምስል አሊያም ጹሁፍን ወደ ንቅሳት መቀየር ይቻላል ይላል።
በብዛት ወደ እሱ የሚመጡ ሰዎች ሰውነታቸው ላይ እንዲያርፍ የሚርጡት ይዘት ሐይማኖታዊ መሆኑን ይናገራል። በተጨማሪም ጥንዶች ፍቅራቸውን ለመግለጽ ተመሳሳይ ንቅሳት ወይም አንዱ የሌላውን ስም ይነቀሳሉ።
የእናታቸውን ወይም የአባታቸውን ምስል ወይም ስም የተነቀሱ ደንበኞች እንዳሉት የሚጠቅሰው ሔኖክ፤ በሌላ በኩል መስቀል፣ የቅዱሳን ሥዕሎችና መሰል ሐይማኖታዊ ይዘቶች በብዛት እንደሚዘወተሩ ያስረዳል።
ብዙዎች ንቅሳትን "የሚወዱትን ነገር መግለጫና ማሳያ አድርገው ነው የሚያዩት" ሲል ይጠቅሳል።
ሳምራዊት የግራ እጇ ከክንዷ በታች ያለው ክፍል ሙሉ በሙሉ በንቅሳት የተሸፈነ ነው።
"ስለ ወደደኝ አዳነኝ" እና "Be Happy" የሚሉ ጽሁፎች፣ ሳቅን የሚገልጽ የስሜት ነጸብራቅ ምስል (emoji)፣ አበባ እንዲሁም ሌሎች ምስሎች አሉ።
ደረቷ ላይ "blessed" የሚል ጽሁፍና አንገቷ ላይ ደግሞ መስቀል ተነቅሳለች።
ኤልዜር የደረቱ አብዛኛው ክፍል ንቅሳት ያረፈበት ሲሆን፤ የነብርና ንስር ምስሎችን ነው የተነቀሰው። ዮሴፍ ደግሞ ሰዓት፣ አበባ፣ ኮምፓስና መሰል ምስሎችን በቀይና ጥቁር ቀለሞች በእጆቹ ላይ ተነቅሷል።
ሳምራዊት ለሐይማኖቷ ያላትን ፍቅር ለመግለጽና ውስጧ ያለውን የተለያየ ሰሜት ለማንጸባረቅ እንደተነቀሰች ትገልጻለች። ዮሴፍ እና ኤልኤዘር ውስጣቸው የሚያምንበትና የሚወዱት ሐሳብ ሰውነታቸው ላይ እንዲታይ በማለም ነው አካላቸውን በንቅሳት የሸፈኑት።
በተለይ ኤልኤዘር ለቤተሰቦቹ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ መነቀሱን ተናግሯል።
እነ ሳምራዊት በጠቀሷቸው ምክንያቶች ይነቀሱ እንጂ ሰውነታቸው ላይ ያለ ጠባሳን ለመሸፈን ወይም ባህላዊ ንቅሳቶችን ወደ ዘመነኛ ለመቀየር ወደ ንቅሳት ቤቶች የሚያመሩ ሰዎች እንዳሉም ሔኖክ ይገልጻል።

የፎቶው ባለመብት, YOSEPH
የንቅሳት ገበያ
ኤልኤዘር ንቅሳቱን በተለያየ ጊዜ ማድረጉን ያስረዳል። ለዚህም እስከ 20 ሺህ ብር አውጥቷል።
ሳምራዊት ደግሞ 15 ሺህ ብር በመክፈል ነው ንቅሳቷን ያሠራችው።
ዝቅተኛው የንቅሳት ርዝመት አምስት ወይም ስድስት ሴንቲ ሜትር እንደሚረዝምና 500 ብር እንደሚያስወጣ ሔኖክ ይገልጻል።
ንቅሳቱ ከፍ እያለ ሲሄድ ዋጋ እንደሚጨምር እንዲሁም ጀርባ ላይ የሚሠሩ ንቅሳቶች በአንድ ጊዜ እንደማያልቁና እስከ ሦስት ቀናት ሊፈጁ እንደሚችሉ ተናግሯል። ይህም እስከ 15 ሺህ ብር የሚወጣበት ነው።
ታዲያ ይህ ሥራ ዋና የገቢ ምንጬ ነው የሚለው ሔኖክ "በየቀኑ ሥራ አለ" ሲል አስረድቷል።
ንቅሳት ለመሥራት የሚውሉ መሣሪያዎች ከዘመኑ ጋር እየተጓዙ ነው የሚለው የንቅሳት ባለሙያው፤ ግብዓቶችን አገር ውስጥ ማግኘት ግን ፈታኝ መሆኑን እና የንቅሳት መርፌ ሳይቀር ከውጪ አገራት እንደሚገባ ይገልጻል።
"ንቅሳት ላይ ከቴክኖሎጂው በላይ የአርቲስቱ ጉዳይ [የባለሙያው አቅም] ነው ትልቁ ነገር" ሲልም ጨምሯል።
የተመልካቾች አስተያየት እና ልዩ ገጠመኞች
ዮሴፍ ንቅሳቴን ሲያዩ "የሚያማትቡ አሉ" ይላል።
ኤልኤዘር ደግሞ "አንዳንድ ሰው የሚያየኝ እንደ ዱርዬ ነው። ባንክ ስገባ አንዳንድ ሰዎች ቦርሳቸውን የሚደብቁበት ጊዜ አለ" ሲል ገልጾታል።
"ሁሉም ሰው አንድ አይደለም። ወጣቶቹ ይወዱታል። 'በጣም ያምራል' ይላሉ። ሌላው ደግሞ 'ኔጌቲቭ' አስተያየት ነው የሚሰጠው። 'ለምን እንዲህ አደርግሽ?' 'በሐይማኖት አይፈቀድም' ይላሉ" ያለችው ደግሞ ሳምራዊት ናት።
የንቅሳት ባለሙያው ሔኖክም በሥራው ብዙ ነገሮች እንደሚገጥሙት ይገልጻል።
ፍቅረኞች ወይም ባለትዳሮች ፍቅራቸውን 'ለማጠንከር' በማሰብ ለመነቀስ ወደኛ ይመጣሉ የሚለው ሔሄኖክ፤ ከተሠራላቸው በኋላ ግን ተመልሰው የሚመጡ እንዳሉ ጠቅሷል።
"ይመጡና ይሄን ነገር አልፈለኩትም። የዚያን ጊዜ በደንብ አላሰብኩበትም። ይሄን ነገር ማጥፋት እፈልጋለሁ ይላሉ። ያው ማጥፋት ከባድ ስለሆነ በሌላ ዲዛይን ይሸፈናል።"
በሌላ በኩል ፊታቸው ላይ ንቅሳት ለማሠራት መጥተው እድሜያቸው ትንሽ ከሆነ "በኋላ እንዳይጸጽታቸው" ብለን እንመክራለንም ብሏል።
"አንዳንዴ ሰዎች ንቅሳተቱን ሳይጨርሱ የሚሄዱበት አጋጣሚ አለ - አመመኝ በሚል" ሲልም ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Samrawit
አንዱን አጋጣሚ ሲያስታውስ፤ አንድ ደንበኛው "የቅዱስ ሚካኤልን ምስል ጀርባው ላይ ለመነቀስ መረጠ" ይላል። እናም ንቅሳቱ ተጀመረ።
"ሥዕሉ መልአኩ ሰይጣኑን ሲረግጥ የሚያሳየው ነው። እኛ ከሥር እየሠራን ነው ወደ ላይ የምንሄደው። ሰይጣኑን ወደ ማገባደድ ደርሰን ወደ ላይ እየወጣን ስንሄድ 'በቃ አልቻልኩም ይቅርብኝ' አለ። ለመጨረስ በተከታታይ ብደውልለትም አልመጣም። እስካሁን ሰይጣኑን ይዞ ነው የሚዞረው" ሲል ያስታውሳል።
ንቅሳቱ ሲሠራ በሚፈጠረው ህመም ምክንያት ንቅሳት ጀምረው ከሚያቋርጡ በተቃራኒው የንቅሳቱ መሣሪያ በሚፈጥው መጠነኛ ህመም 'እንደሚደሰት' ዮሴፍ አስረድቷል።
ኤልኤዘር ደግሞ "አንድ ጊዜ ፀበል ለጠመቅ ሄጄ ቄሱ አልጠምቅህም ብለውኝ ነበር [ንቅሳቱን አይተው]" ብሏል።
በሌላ በኩል ዮሴፍ "ሰዎች እንደ ቁም ነገረኛ ስለማይቆጥሩኝ፤ ሥራ ቦታ 'ታቱ' እንዳለኝ የማያውቅ ብዙ ሰው አለ" ሲል ገልጿል።
ሳምራዊት በመነቀሷ ከቤተሰቧ አሉታዊ አስተያየት እንዳልገጠማትና እንዲያውም ስትነቀስ 15 ሺህ ብሩን ቤተሰቧ እንደከፈለላት ስትናገር፤ ከዚህ በተቃራኒ ኤልኤዘርና ዮሴፍ ቤተሰቦቻቸው ብዙም በአወንታዊ መንገድ አልተቀበሏቸውም።
ንቅሳት እና ጤና
የቆዳና የአባላዘር በሽታዎች ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶክተር ድጋፌ ጸጋዬ "ዘመናዊም ይሁን ባህላዊ ንቅሳት ሹል በሆኑ ነገሮች እየወጉ ቀለምን ቆዳ ውስጥ በመጨመር ጌጦችን የመፍጠር ልምድ ነው ብለን ልንገልጸው እንችላለን" ሲሉ ያስረዳሉ።
ታዲያ ይህ ልምድ ከጤና አኳያ ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮች አሉትም ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ድጋፌ ገለጻ፤ ንቅሳት ቋሚ ሲሆን ሰዎች ግን ቀድመው ለንቅሳት የተነሱበት ፍላጎትና ስሜት በጊዜ ብዛት ሊቀየር ይችላል። በዚህም ምክንያት የተነቀሱ ሰዎች ከ40 ዓመታቸው በኋላ የሚጸጸቱበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።
በሌላ በኩል "ንቅሳት ያለበት ሰው ደም እንዲሰጥ አይመከርም" ያሉት ሀኪሙ፤ ለዚህም ምክንያቱ የንቅሳት መሣሪያዎች ለተላላፊ በሽታ ስለሚያጋልጡ ነው ብለዋል።
ንቅሳት የቆዳ መቆጣት [allergic reactions] ሊፈጥር እንደሚችል ዶ/ር ድጋፌ ጠቅሰዋል።
"የሰውነት አለርጂው ከብዙ ጊዜ በኋላ ይመጣል። ከተነቀሱ ከሳምንታት ብሎም ከ10 ወይም ከ15 ዓመታት በኋላ የቆዳ መቆጣት፣ የማሳከክ ወይም የማበጥ ስሜትን ሊያመጣ ይችላል" ብለዋል።
ንቅሳት የሚደረግበት ስፍራና የመሣሪያው ንጽህና ካልተጠበቀ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ሊዳርግም ይችላል።
"ንቅሳት ያደረገ ሰው ኤምአርአይ የሚባለውን ምርመራ ማድረግ ቢፈልግ እንደ ንቅሳቱ አይነትና የቀለም አይነት ንቅሳቱ ባለት ቦታ ላይ የቃጠሎ ቁስል ሊያጋጥም ይችላል" ሲሉም ያክላሉ።
ቋሚ ንቅሳት መጥፋት ይችላል?
አዎ መጥፋት ይችላል።
"አብዛኛውን ንቅሳት በሌዘር [በጨረር] ማሽን ማጥፋት የሚቻልበት ዕድል አለ" ሲሉ ገልጸዋል - ዶ/ር ድጋፌ።
ሕክምናው የብርሃንን ኃይል ወደ ሙቀት በመቀየር የሚሠራ መሆኑን የሚስረዱት ሐኪሙ፤ ጨረሩ ቆዳው ውስጥ ያለውን ቀለም በመሰባበር በደም አማካይነት እንዲወገድ ያደርጋል ብለዋል።
ሕክምናው ተከታታይ ሲሆን፤ ለዘመናዊ ንቅሳት ከ6 እስከ 10 ጊዜ ቢሰጥ "ከፍተኛ ለውጥ ሊመጣ የሚችልበት አጋጣሚ አለ" ብለዋል - ቆዳን ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ባይመልሰውም።
ሕክምናው በእያንዳንዱ የክትትል ዙር እስከ 2500 ብር ሊያስወጣ እንደሚችል የሚገልጹት ሐኪሙ፤ ሰዎች ንቅሳት ከማሠራታቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡበት መክረዋል።












