ቬትናም 13 ሚሊየን የሚገመተ የአንድ ከተማ ነዋሪዎችን በሙሉ ልትመረምር ነው

ቬትናም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቬትናም ያጋጠማትን አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ለመቆጣጠር በማሰብ ለሆ ቺ ሚኒ ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ የኮቪድ ምርመራ ለማድረግና አዲስ ጠበቅ ያለ የአካላዊ ርቀት መመሪያዎችን ተግባራዊ ልታደርግ እንደሆነ አስታወቀች።

ቬትናም የወረርሽኙን ስርጭት በመቆጣጠር ትልቅ ስኬትን ማግኘት የቻለች አገር ብትሆንም በቅርብ ሳምንታት ግን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመሩ ተገልጿል።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ በአገሪቱ በጣም አስጊ የሆነ አዲስ የኮሮናቫይረስ አይነት መኖሩን ባስልጣናት አስታውቀዋል።

መንግሥት እንደሚለው አዲሱ የቫይረስ አይነት በሕንድ እና ዩናይትድ ኪንግደም ከታዩት የቫይረሱ ዝርያዎች የተቀላቀለ ሲሆን በቀላሉ በአየር መተላለፍ የሚችል ነው።

በአጠቃላይ ቬትናም እስካሁን ከ7 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ያስታወቀች ሲሆን 47 ሰዎች ደግሞ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሕይወታቸው አልፏል። ነገር ግን በቅርብ ሳምንታት የታየው ቁጥር ከአጠቃላዩ ቁጥር ግማሹን ይይዛል።

በሆ ቺ ሚኒ ከተማ የተከሰተው አዲሱ የቫይረሱ አይነት በብዛት የሚገኘው በክርስትና እምነት ተከታዮች በሚያዘወትሯቸው አብያት ክርስቲያናት አካባቢ ሲሆን እስካሁንም 125 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በከተማዋም ከተመዘገቡ ቁጥሮች ይሄኛው በጣም ከፍተኛ ነው ተብሏል።

ቫይረሱ በብዛት ተሰራጭቶ በተገኘባቸው የከተማዋ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ሁሉም ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም እራሳቸውን አግልለው እንደሚገኙ ተገልጿል።

ባለስልጣናትም በሆ ቺ ሚኒ ከተማ የሚኖሩ 13 ሚሊየን ሰዎችን በሙሉ ለመመርመር እቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ነገር ግን በቀን 100 ሺ ሰዎችን መመርመር በሚያስችል አቅም ሁሉንም ሰው ለመመርመር ከአራት ወራት በላይ ሊፈጅ እንደሚችል ተጠቁሟል።

በከተማዋ ከሚደረገው ነዋሪዎችን የመመርመር ተግባር በተጨማሪ ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ለ15 ቀናት የሚቆይ ጠበቅ ያለ አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ መመሪያ ተላልፏል።

ሱቆች፣ ባርና ሬስቶራንቶች ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ሲሆን ለጊዜው ደግሞ ማንኛውም አይነት ሀይማኖታዊ ስነ-ስርአቶች ታግደዋል።

''ከ10 ሰዎች በላይ የሚሰባሰቡበት ማንኛውም አይነት ህዝባዊ ሁነት በመላ ከተማዋ ተከልክሏል። ነገር ግን እንደውም ቁጥሩን ወደ 5 ዝቅ ለማድረግ እየታሰበ ነው'' ሲሉ የአገሪቱ ጤና ኃላፊ ተናግረዋል።

ኮሮናቫይረስ ባሳለፍነው ዓመት ከቻይና ተነስቶ ዓለምን ሲያዳርስ ቀድመው እርምጃ ከወሰዱት አገራት መካከል አንደኛዋ የሆነችው ቬትናም፤ ፈጣንና ውጤታማ የመከላከል ስራዎችን ሰርታለች።