በናይጄሪያ ታጣቂዎች ተማሪዎችን አግተው ወሰዱ

በናይጄሪያ ሰሜናዊ ክፍል ከሚገኝ አንድ እስላማዊ ትምህርት ቤት ታጣቂዎች ተማሪዎችን አግተው መውሰዳቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ።
ታጣቂዎቹ ቴጊና ተብላ በምትጠራው ከተማ ከሚገኘው ትምህርት ቤት ትናንት እሁድ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ ተማሪዎች መውሰዳቸውን ባለስልጣናቱ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አንድ መምህር 150 ተማሪዎች መወሰዳቸውን ሲናገር ሌሎች ደግሞ ታፍነው የተወሰዱት ተማሪዎች ቁጥር ከ200 በላይ ነው ይላሉ።
ከጥቂት ወራት በፊት 300 ሴት ተማሪዎች በታጣቂዎች ታግተው ተወስደው ነበር። በወቅቱ ታግተው ከተወሰዱ ተማሪዎች መካከል እስካሁን ያልተለቀቁ ተማሪዎች አሉ።
ዚስ ደይ የተባለ ድረ-ገጽ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ታጣዊዎቹ በበርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ ተኩስ ከፍተዋል።
ታዳጊዎቹ ታፍነው የተወሰዱበት ትምህርት ቤት እድሜያቸው ከ6-18 ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምር ነው ተብሏል።
የአከባቢው ባለስልጣናት ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ ሁለት ሰዎች በጥይት ከተመቱ በኋላ የአንዱ ሕይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።
የቢቢሲዋ ዘጋቢ ማዬኒ ጆነስ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሰሜናዊ የአገሪቷ ክፍል በሚገኙ ግዛቶች ውስጥ ተማሪዎችን አግቶ ገንዘብ የመጠየቅ ወንጀል እየተበራከተ ነው ትላለች።
እነዚህ ተማሪዎች የታገቱት በሰሜናዊ ናይጄሪያ በምትገኘው ካዱና ግዛት ዩኒቨርሲቲ 14 ሰዎች ታግተው ቆይተው የመለቀቃቸው ዜና ከተሰማ በኋላ ነው።
ባለፉት ስድስት ወራት በሰሜናዊ ናይጄሪያ ክፍል ቢያንስ ስድስት ጊዜ ያህል የእገታ ወንጀሎች ተፈጽመዋል።
የትምህርት ተቋማት ላይ ባነጣጠሩ እገታዎች ከ800 በላይ ተማሪዎች እና ሠራተኞች ታግተዋል።
እአአ 2014 ቺቦክ ተብላ ከምትጠራው ከተማ 276 ሴት ተማሪዎች በቦኮ ሃራም ቡድን ታፍነው የመወሰዳቸው ዜና በርካቶችን ያነጋገር ክስተት ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጸሙ ያሉ እገታዎች ግን በአደጋኛ የወንጀለኛ ቡድኖች አማካኝነት የሚፈጸም ሳይሆን አይቀርም ይባላል።












