አሜሪካ ከዴንማርክ ጋር በማበር የአውሮፓ ፖለቲከኞችን ሰልላች ተብላ ተወቀሰች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዴንማርክ የስለላ ድርጅት አሜሪካ የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንግላ ሜርክልን ጨምሮ በአውሮፓ ፖለቲከኞች ላይ ስለላ እንድትፈፅም ረድቷል ሲሉ የዴንማርክ መገናኛ ብዙሃን ዘግቡ።
መገናኛ ብዙሃኑ እንደሚሉት ስለላው የተፈፀመው በፈረንጆቹ ከ2012 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ነው።
የዴንማርክ መከላከያ ደህንነት መሥሪያ ቤት ከአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር መረጃ ሰብስበዋል ብሏል የዴንማርክ ብሔራዊ ራድዮ ጣቢያ።
ስለላው ተካሄደ የተባለው እንደ ጀመርን፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን እና ኖርዌይ ባሉ ሃገራት ባለሥልጣናት ላይ ነው።
ተመሳሳይ ወቀሳዎች በፈረንጆቹ 2013 ቀርበው እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ የአሜሪካ ስለላ ሚስጢሮችን ለዓለም ይፋ ያደረገው ኤድዋርድ ስኖውደን የአሜሪካው ስለላ ድርጅት የጀመርኗ መራሂተ መንግሥት አንግላ ሜርክልን ስልክ ጠልፏል ብሎ ነበር።
ይህ ወቀሳ በቀረበ ወቅት ዋይት ሃውስ መረጃውን በቀጥታ አላስተባበለም፤ ነገር ግን የሜርክል ስልክ አልተጠለፈም ወደፊትም አይጠለፍም ብሎ ነበር።
ጀርመር አውሮፓ ውስጥ ካሉ የአሜሪካ ቅርብ ወዳጆች ቀንደኛዋ ናት።
አሁን በበርካታ የአውሮፓ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ እየተሰራጨ ያለው ዜና የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲ የበርካታ ፖለቲከኞችን የፅሁፍ መልዕክት ልውውጥና የስልክ ልውውጥ ሰምቷል ይላል።
ይህን ለማድረግ ደግሞ ከዴንማርክ ስለላ ድርጅት ጋር ተባብሯል ሲሉ መገናኛ ብዙሃን ይዘግባሉ።
"ኦፕሬሽን ደንሃመር" የተሰኘ ስም ተሰጥቶት ነበር የተባለው ይህ የስለላ ተግባር አሜሪካ በስልክ መስመር አማካይነት መረጃዎችን እንድትሰበስብ ረድቷል ብሏል የዳኒሽ ራድዮ ጣቢያ።
ራድዮ ጣቢያው የሠራው የምርመራ ዘገባ ከዴንማርክ ስለላ ድርጅት ጋር ግንኙነት ያላቸው ዘጠኝ የመረጃ ምንጮችን ተጠቅሞ ነው።
ከአንግላ ሜርክል በተጨማሪ የያኔው የጀመርን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ዋልተር እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ፒር ስታይንብሩክም ስልካቸው ተጠልፎ ነበር ተብሏል።
የዴንማርክ መከላካያ ሚኒስቴርም ሆነ የስለላ ድርጅቱ እስካሁን በቀረበው ወቀሳ ላይ ያሉት ነገር የለም።
ዘገባዎቹን ተከትሎ ኤድዋርድ ስኖውደን የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን "በወቅቱ በስላለው ላይ ተሳትፎ ነበራቸው" ሲል ወቅሷቸዋል። ባይደን በወቅቱ ምክትል ፕሬዝደንት እንደነበሩ አይዘነጋም።
የአሜሪካው ስለላ ድርጅት [ሲአይኤ] የቀጠረው ድርጅት ውስጥ ይሰራ የነበረው ስኖውደን አሜሪካ ሕዝቧን በስልክ ትሰልላች ሲል መረጃ አጋርቶ ሃገር ጥሎ መጥፋቱ ይታወሳል።
አሜሪካ ሰውዬውን የመንግሥት ንብረት በመስረቅ፣ ያልተፈቀደለትን የደህንነት መረጃ በማጋራት እንዲሁም ምስጢራዊ መረጃዎችን ይፋ በማድረግ ወንጀል ከሳዋለች።
ስኖውደን በአሁን ወቅት ሩስያ ውስጥ በጥገኝነት ይኖራል።












