ናኦሚ ኦሳካ ለመገናኛ ብዙሃን አልናገርም በማለቷ ከውድድሮች ልትታገድ ትችላለች ተባለ

ናኦሚ ኦሳካ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ናኦሚ ኦሳካ

የዓለም ቁጥር ሁለቷ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ናኦሚ ኦሳካ ለመገናኛ ብዙሃን ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆኗን ከቀጠለች የፈረንሣይ ኦፕንን ጨምሮ ወደፊቱ ከሚደረጉ የግራንድ ስላም ውድድሮች እንደምትባረር አዘጋጆቹ ተናግሩ።

ጃፓናዊቷ ኦሳካ ባለፈው ሳምንት የአዕምሮ ጤንነቷን ለመጠበቅ ስትል በሮላንድ ጋሮስ (የፈፈረንሳይ ኦፕን ሌላኛው ስም) ውድድር ወቅት ምንም ዓይነት መግለጫ እንደማትሰጥ ገልጻለች።

እሑድ ሮማኒያዊቷን ፓትሪሺያ ማሪያ ቲግን በውድድሩ የመጀመሪያ ዙር አሸንፋ መግለጫ ባለመስጠቷ 15,000 ዶላር ተቀጥታለች፡፡

የዓለም ቁጥር ሁለቷ ውድድሩን 6-4 7-6 (7-4) አሸንፋለች፡፡

የአራቱ ግራንድ ስላም አዘጋጆች በጋራ በሰጡት መግለጫ ኦሳካ፤ “ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት እና ወደፊቱ ከግራንድ ስላም ውድድሮች ልትታገድ ትችላለች” ብለዋል፡፡

ኦሳካ እሁድ ዕለት “ለውጥ ሰዎችን ምቾት እንዳይኖራቸው ያደርጋል” ስል በትዊተር ገጿ አስፍራለች።

ኦሳካ ሃሳቧን ማስታወቋን ተከትሎ አዘጋጆቹ የ23 ዓመቷ የቴኒስ ተጫዋች ሃሳቧን እንደገና እንድታጤን የጠየቁ ሲሆን የጤንነቷን ሁኔታ ለመፈተሽ ያደረጉት ሙከራም አልተሳካም፡፡

ከኦሳካ “የምላሽ አለማግኘት” በኋላ ድጋፍ እንደሚሰጣት እና “ግዴታዋንም አስታሰውሰው” የጽሑፍ መልዕክት ሰደውላታል፡፡

“ከግራንድ ስላም ህጎች ዋነኛው ተጫዋቾች ምንም ውጤት ያስመዝግቡ ከሚዲያ ጋር የመሠራት ሃላፊነታቸው ነው። ይህም ተጫዋቾቹ ለስፖርቱ፣ ለደጋፊዎች እና ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚወስዱት ሃላፊነት ነው” ብሏል መግለጫው፡፡ .

“ናኦሚ ኦሳካ በውድድሩ ወቅት የሚዲያ ግዴታዎቿን ችላ ማለቷን ከቀጠለች ለተጨማሪ የሥነ ምግባር ጥሰት መዘዞች ራሷን ታጋልጣለች” ብሏል።

“ተደጋጋሚ ጥሰቶች ከውድድሩ መታገድን ከባድ የወንጀል ምርመራን ጨምሮ ከፍተኛ ቅጣቶችን ያስከትላል። ለወደፊቱም ከግራንድ ስላም ውድድሮች እገዳን ሊያስከትል ይችላል።“

አክሎም ህጎች ያሉት “ሁሉም ተጫዋቾችን በአንድ ዓይን እንዲታዩ ለማድረግ” ነው ብሏል፡፡

እንዴት እዚህ ደረጃ ተደረሰ?

የመገናኛ ብዙሃን መግለጫዎች በተጫዋቾች የአዕምሮ ጤንነት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በመጥቀስ በፈረንሣይ ኦፕን ወቅት መግለጫ እንደማትሰጥ ኦሳካ ረቡዕ ዕለት አሳወቀች፡፡

ተጫዋቾች ከሽንፈት በኋላ ለጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡ መጠበቁን “እየወደቀ ያለን ሰው ከኋላ የመርገጥ ያህል ነው” ስትል አስረድታለች፡፡

በማህበራዊ ድር አምባር ባስተላለፈችው መግለጫ “ብዙ ጊዜ ሰዎች ለአትሌቶች የአዕምሮ ጤንነት ምንም እንደማይጨነቁ ይሰማኛል። ይህ እውነት መሆኑን ጋዜጣዊ መግለጫ ስመለከት ወይም ስሳተፍ ያየሁት ነው” ብላለች፡፡

“ብዙ ጊዜ እዚያ ቁጭ ብለን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የተጠየቅነውን ጥያቄዎች ወይም በአዕምሯችን ጥርጣሬን የሚጭሩ ጥያቄዎችን እንጠየቃለን። እናም እኔ ለሚጠራጠሩኝ ሰዎች ራሴን አላስገዛም፡፡“

በግራንድ ስላም ህግ ተጫዋቾች የመገናኛ ብዙሃን ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው እስከ 20,000 ዶላር ሊቀጡይችላሉ።

የሴቶች ቴኒስ ማህበር እንደሚለው በውድድር ወቅት ተጫዋቾቹ ለመገናኛ ብዙሃን የመናገር “ስፖርታዊ እና የአድናቂዎቻቸው ኃላፊነት አለባቸው።"

የቴኒስ ተጫዋቾችን ጨምሮ ሌሎች ስፖርተኞች ብዙዎቹ ለመገናኛ ብዙሃን መናገር “የሥራው አካል” መሆኑን ቢቀበሉም የኦሳካን አቋም አድንቀዋል።

ኦሳካ ከድሏ በኋላ የተለመደውን የሜዳ ላይ ቃለ-መጠይቅ አድርጋለች፡፡

“በአሸዋ ሜዳ ያለኝ እንቅስቃሴ እየተሻሻለ ያለ ነው፡፡ ብዙ ግጥሚያዎችን ካደረኩኝ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች፡፡