የአውሮፓ ታላላቅ አሰልጣኞች መልቀቅ እና ቀጣይ እጣ ፈንታቸው

የአውሮፓ ታላላቅ አሰልጣኞች መልቀቅ እና ቀጣይ እጣ ፈንታቸው

አንቶኒዮ ኮንቴ ሴሪ አን ካሸነፈ በኋላ ኢንተር ሚላንን በቃኝ ብሏል። ዚኔዲን ዚዳን ከሪያል ማድሪድ ኃላፊነቱን ሲለቅ ቶተንሃም የፓሪስ ሴንት ዠርሜኑን አለቃ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖን ለማስኮበልል እየሞከረ ነው።

የሊግ 1 አሸናፊነት ክሪስቶፍ ጋልቲየርን በሊል ማቆየት አልቻለም። ጁቬንቱሶች አንድሪያ ፒርሎን በማሰናበት በማሲሚሊያኖ አሌግሪ ሊተኩት እየሠሩ ነው።

በጀርመን ዮሃንስ ፍሊክ ከባየር ሙኒክ መነሳት ተመሳሳይ ውሳኔ በሌሎች ክለቦችም ዘንድ እንዲተገበር መንገድ ከፍቷል።

የ2020 - 21 የውድድር ዘመን አቧራ ገና አልሰከነም። ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ብዛት ያላቸው ታላላቅ አሰልጣኞች ከሥራቸው ሲለቁ ተመልክተናል።

ከገንዘብ ነክ ጉዳዮች እስከ አድካሚው ዓመት ያለውን ዝርዝር ሁኔታ የቢቢሲ ሬዲዮ 5 ባለሙያዎች ለምን እንደሆነ ይተነትኑታል።

"በከፍተኛ ሁኔታ የተፈጠሩ አለመግባባቶች"

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የእግር ኳስ ክለቦችን ፋይናንስ አሽመድምዷል። ኬፒኤምጂ እንደተባለው የገበያ ኩባንያ ከሆነ በአውሮፓ ኃያላኑ 32 ክለቦች ከየካቲት 2020 ጀምሮ 6.1 ቢሊዮን ዩሮ አጥተዋል።

በጀርመን ፍሊክ ባየርን ለቀቀ። ጁሊያን ናጌልስማን በቦታው ተተካ። ጄሲ ማርች ደግሞ አር ቢ ላይፕዚግን በመረከቡ በርካታ ለውጦች ተከታትለው መጡ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በጣሊያን፣ በስፔን፣ በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ ያለው ተመሳሳይ ታሪክ ነው።

ጀርመናዊው የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ራፋኤል ሆኒግስቴይን በቢቢሲ ራዲዮ 5 ቀጥታ ስርጭት ላይ "መልቀቂያዎቹ የሚያመሳስላቸው በኮቪድ-19 ወቅት ስለ ገንዘብ ብዙ ውስጣዊ ክርክሮችን በመመልከታችን ነው" ብሏል።

"ከእነዚህ አሰልጣኞች ብዙዎቹ ለቀዋል። ምክንያቱም ለሌላ ሥራ ለመሰለፍ ሳይሆን ስለበቃቸው ነው" ሲል ተናግሯል።

አክሎም "ከዚህ ቀደሙ በተለየ በእነዚህ ትላልቅ ክለቦች ትላልቅ አሰልጣኞች በዚህ ቁጥሮች ሲለቁ አላየንም" ብሏል።

"ፍሊክ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ከፍተኛ አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ ነው የለቀቀው። ምክንያቱ ደግሞ ኮቪድ-19 ነው። ፍሊክ የሚፈልገውን ያህል ገንዘብ ሙኒክ ማውጣት አልቻለም። በዚህም አለመግባባቱ ተጀመረ" ሲል አስረድቷል።

በላሊጋው 2ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሪያል ማድሪድ በኬፒኤምጂ ጥናት የአውሮፓ ውዱ ክለብ በመሆን አጠናቋል። ዚዳን ግን በቦርዱ እና በፕሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ስለመደገፉ አልተሰማውም ሲል የስፔን እግር ኳስ ባለሙያው ጊየም ባላጌ አስታውቋል።

ኮንቴ በ11 ዓመታት የመጀመሪያውን የጣሊያን ዋንጫ ለክለቡ ቢያሳካም በኢንተርም ተመሳሳይ ታሪክ ነው ያለው። ምክንያቱም በክለቡ የፋይናንስ ችግር የተነሳ በዚህ ክረምት የደመወዝ ክፍያን በ 20 በመቶ ለመቀነስ ተዘጋጅቷል።

ጣሊያናዊው ጋዜጠኛ ጋብሪኤል ማርኮቲ "ኮንቴ ገንዘብ ፈለገ፤ ጥያቄዎችንም አቀረበ። ነገር ግን አንድ ወይም ሁለት ታላላቅ ተጫዋቾችን ከማግኘት ይልቅ አንድ ወይም ሁለት ታላላቅ ተጫዋቾችን መሸጥ ሊኖርበት ነው" ብሏል።

"ስሜቱ ተለውጧል፡፡ ፔፕ ጋርዲዮላ ወይም የርገን ክሎፕን ካልሆንክ እነዚያን ጥያቄዎች ማንሳት በጣም ከባድ ነው" ይላል፡፡

ማርኮቲ አክሎም "አዳዲስ ተጨዋቾችን ከመግዛት ይልቅ አዲስ አሰልጣኝ ማምጣት ይረክሳል። በግልጽ እንደሚታየው ተያያዥ ምላሽ ስለመኖሩ አይካድም። አብዛኛው ከድህረ ኮሮናቫይረስ ገንዘብ፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው" ብሏል፡፡

"ለዚህም ነው ዚዳን ከማድሪድ የለቀቀው፣ ኮንቴ ኢንተርን የተሰናበተው። ይህ የዝውውር መስኮት ለአሰልጣኞች እና ለተጫዋቾች በጣም የተለየ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው" ሲል ያስረዳል፡፡

አንዳንዶቹ ደክመዋል፣ ሌሎች ደግሞ አዲስ ፈተናዎች አስፈልጓቸዋል

ያለፈው ዓመት በወረርሽኙ ከተስተጓጎለ በኋላ በመላው አውሮፓ ያሉ ክለቦች በተጨናነቀ የጊዜ ሰሌዳዎች እንዲጫወቱ ማስገደዱን ተከትሎ ውስጣዊ ውጥረቶች መኖራቸው የተጠበቀ ሊሆን ይችላል፡፡

እንደ ኮንቴ ያሉት አንዳንዶቹም ችግሮች ቢኖሩም፣ በዝውውር ገንዘብ ላይ አለመግባባት ቢፈጠርም ስኬት አስመዝግበዋል።

ዚዳን ዋንጫ ማንሳት ቢሳነውም በዕድሜ የገፋውን የሪያል ቡድን ይዞ የላሊጋው ሻምፒዮንነትን ለጥቂት ሲያጣ በቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ደርሶ በቼልሲ ተሸንፏል።

የፈረንሣዊው የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ጁሊየን ሎረን እንደተናገረው "በተፈጠረው ነገር በሙሉ ይህ ለዚዳን ልዩ ዓመት ነበር። በኮሮናቫይረስ ተያዘ፡፡ ቡድኑን እስከደረሰበት ደረጃም ለማብቃት ችሏል።"

"ምናልባትም ከዚህ የተሻለ ማድረግ ከባድ እንደሚሆን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ብዙዎች አሰልጣኞች ሲለቁ በልባቸው ውስጥ ያለው ይህ ነው - 'በዚህ ዓመት ካደረግነው የበለጠ ልንሠራ እንችላለን?' የሚል፡፡

"ጋልቲየ በሚቀጥለው ዓመት ሊል የሊግ 1 ን በድጋሚ የሚያሸንፍበት ዕድል እንደሌለ አስቦ ይሆናል። ሌሎች አማራጮች እያሉ ለምን ይቆያሉ? ለኮንቴም ምናልባት ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፡፡"

ባላጌ አክሎም "ትላልቅ ክለቦች አሰልጣኞቻቸውን እየቀያየሩ ነው። ትላልቅ ሥራዎች ክፍት ስለሆኑ ለመመረጥ ዝግጁ የሆኑ ሁለት ወይም ሦስት አሰልጣኞች አሉ" ብሏል፡፡

"በእርግጥ ዚዳን ወደ ሌላ ሥራ እንደሚሄድ ቢጠበቅም፤ ዝሎና ተዳክሞ ነበር፡፡ ብዙ አሰልጣኞችንም ነክቷል።"

ማን ወዴት እያመራ ነው?

በጣም ስመ ገናና የሆኑ አሰልጣኞች ከአንዱ ወደ ሌላው ክለብ በመንቀሳቀስ ላይ በመሆናቸው ማን ወዴት ያመራል የሚሉ ግምቶች እጥረት የለም፡፡

ኮንቴ ከሪያል ማድሪድ እና በፕሪሚየር ሊጉ ደግሞ ክፍት ከሆነው የቶተንሃም ሥራ ጋር ስሙ ተገናኝቷል፡፡

የቀድሞው አሰልጣኙ ፖቸቲኖን በተመለከተ ስፐርስ ከፓሪስ ሴንት ጀርሜን ጋር ግንኙነት አድርገዋል። ማርኮቲ በበኩሉ ለቢቢሲ ራዲዮ 5 እንደገለጸው ፖቸቲኖ የማድሪድ ዋነኛ ዒላማ ነው፡፡

ሲሞኔ ኢንዛጊ ሐሙስ ዕለት ከሌላው የሴሪ ኤ ቡድን ላዚዮ መሰናበቱን ተከትሎ በኢንተር የኮንቴ ተተኪ ሆኖ የተሰለፈ ይመስላል፡፡

የቀድሞው አለቃቸውን አሌግሪን እንደሚተኩ የሚነገርላቸው ጁቬንቱሶች የሚያሰናበቱት አንድሪያ ፒርሎ መጨረሻ ምን እንደሚሆን ለመገመት ይከብዳል፡፡

ሊልን ለመልቀቅ "ጊዜዬ አሁን ደርሷል" የሚል ጥልቅ እምነት ያለው ጋልቲየ በቀጣይ ከኒስ እና ሊዮን አሰልጣኝት ጋር ስሙ ተያይዟል። የቀድሞው የዎልቭሶች አለቃ ኑኖ ኤስፒሪቶ ሳንቶም እንዲሁ አዲስ ክለብ እየፈለገ ነው፡፡