ወደፊት እግር ኳስ ተጫዋቾች 'ቴስታ' መምታት ይከለከሉ ይሆን?

ዴቪድ ሉዊዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዴቪድ ሉዊዝ

ቴስታ ወይም የጭንቅላት ኳስ ወደፊት ከእግር ኳሱ ዓለም ሊወገድ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነጋገሪያ ሆኗል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ጤና ነው። ተመራማሪዎች ኳሰን በጭንቅላት መግጨት ጣጣ አለው እያሉ ነው።

እንግሊዝ ይህን በማስመልከት ሕፃናት እግር ኳስ ሲጫወቱ ቴስታ እንዳይመቱ የሚከለክል ሕግ እያወጣች ነው።

አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው የቀድሞ ተጫዎቾች ከሌሎች በተለየ በጭንቅላት ሕመም የመሞት ዕድላቸው በሦስት እጥፍ የጨመረ ነው።

በዚህ ሃሳብ እግር ኳስ ተጫዎቾችም ይስማማሉ።

የቀድሞው የቶተንሃምና የሃል ሲቲ ተጫዋች ራያን ሜሰን ቴስታ በሚቀጥሉት ከ10 አስከ 15 ዓመታት ባለው ጊዜ ሊቀር ይችላል ይላል።

ሜሰን በ2017 ጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በጊዜ ከእግር ኳስ ሕይወት ራሱን አሰናብቷል።

የ29 ዓመቱ ሜሰን "በሚቀጥሉት ዓመታት ቴስታ ከእግር ኳስ ዓለም መወገድ አለበት ቢባል አልደነቀም" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

ሜሰን እንደሚለው ቴስታን በተመለከተ የሚሠሩ ጥናቶች ከዚህም በላይ በጣም አስደንጋጭ ውጤቶች ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።

"እኔ እግር ኳስ ተጫዋቾች ቴስታ የሚያመጣውን ተፅዕኖ በቅጡ ያወቁት አይመስለኝም። ለዚህ ነው ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ የምለው።"

"በጣም አስጨናቂ ጉዳይ ነው" ይላል ሜሰን ስለጭንቅላት ኳስ ሲያወራ።

"ችግሩ የቴስታን ጉዳት አሁን አናየውም። ጉዳቱ የሚመጣው ከዓመታት በኋላ ነው።"

ቴስታ በእግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ የሚያመጣው ጉዳት ምንድነው የሚለውን ያጠኑት ዶ/ር ዊሊ ስቴዋርት ቴስታ የጭንቅላት ሕመምና የመርሳት በሽታ ሊያስከትል ይችላል ይላሉ።

በፈረንጆቹ 1966 ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫ ያነሳው ኖቢ ስታይልስ ባለፈው ጥቅምት ከመሞቱ በፊት በተደጋጋሚ ኳስን በጭንቅላቱ በመምታቱ ለመርሳት በሽታ እንደተጋለጠ ተናግሮ ነበር።

ከቴስታ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ የአየር ላይ ኳስ በጭንቅላት ለመግጨት በሚደረግ ፍልሚያ የሚከሰተው አደጋ ነው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አርሰናልና ዎልቭስ በነበራቸው ጨዋታ የአርሴናሉ ዴቪድ ሉዊዝና የዎልቭሱ ራዉል ሂሜኔዝ ለጭንቅላት ኳስ ሲሻሙ ተጋጭተው ሂሜኔዝ ክፉኛ ተጎድቶ ነበር።

በወቅቱ ሂሜኔዝ በቃሬዝ ነበር ከጨዋታው የወጣው። ሉዊዝ ደግሞ ጭንቅላቱን በፋሻ አስሮ ጨዋታውን ቀጥሎ ነበር።

እንግሊዛዊው የቀድሞ የፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ አለን ሺረር አርሴናል ሉዊዝን ከሜዳ ማስወጣት ነበረበት ብሎ ትችት መሰንዘሩ አይዘነጋም።

የቀድሞው የቶተንሃም ተጫዋች ያን ቬርቶንገን ከሁለት የውድድር ዘመን በፊት በቻይምፒየንስ ሊግ ጨዋታ የጭንቃላት አደጋ አጋጥሞት ነበር።

ተጫዋቾ የዚህ አደጋ ሕመም ለዘጠኝ ወራት ያህል ይሰማው እንደነበር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተናግሮ ነበር።

ሜሰን ከቼልሲው ተከላካይ ጋሪ ካሂል ጋር ተጋጭቶ ባጋጠመው አደጋ ነው ጉዳት የደረሰበት።

"በሕይወቴ መቆየቴ በራሱ ዕድለኛነት ነው" ይላል።

ከሚቀጥለው ጥር ወር ጀምሮ ክለቦች የጭንቅላት አደጋ ሲያጋጥም ከመደበኛው ቅያሪ በተጨማሪ ሁሉት ተጫዋቾችን መቀየር እንዲችሉ ይፈቀድላቸዋል።

አሁን የቶተንሃም አካዳሚ አሠልጣኝ ሆኖ የሚያገለግለው ሜሰን ግን ይህ ከሚሆን የጭንቅላት ኳስ ሕግ ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት ብሎ ያምናል።

ቴስታ ወደፊት ከእግር ኳስ ዓለም ይወገድ ይሆን? የሚለው ጥያቄ ግን አከራካሪነቱ እንደቀጠለ ነው።