ኮሮናቫይረስ፡ ቱርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሙሉ የእንቅስቃሴ እገዳ ልትገባ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቱርክ በኮሮናቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚሆን የእንቅስቃሴ ገደብ ልትጥል ነው።
ጎዳናዎቹ ተጨናንቀዋል፣ የገበያ ማዕከላትም ሥራ የበዛባቸው ሲሆን ከፍተኛ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴም ይታያል።
ከኢስታንቡል መውጣት የሚፈልጉ ሰዎች ወደ ዋናው የአውቶቡስ መናኽሪያ ሲጎርፉ ሌሎቹ ደግሞ "በአልኮል ሽያጭ እገዳ" ዜና ምክንያት አልኮል ገዝተው እያከማቹ ነው።
ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው እያሻቀበ የመጣውን በኮቪድ-19 የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ቱርክ ከሐሙስ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሙሉ የእንቅስቃሴ እገዳ ልትገባ በማቀዷ ነው።
የተለያዩ የዋትሳፕ ቡድኖች በእገዳው ወቅት ሕይወት ምን እንደሚመስል በሚገልጹ መልዕክቶች ተሞልተዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት ቱርክ ቫይረሱን ለመግታት ባደረገችው እንቅስቃሴ ስኬታማ ተብላ ነበር። በዓለም ጤና ድርጅትም ተሞካሽታ ነበር።
ከአንድ ዓመት በኋላ ግን በአውሮፓ ከፍተኛ በበሽታው የመያዝ ምጣኔ ካለቸው እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጎዱት አገራት መካከል ተመድባለች።
በቱርክ የበሽታው መጠን እንዴት ጨመረ
በወረርሽኙ ምክንያት የአንካራ ከተማ 39 ሺህ ገደማ ሞት ያስመዘገበች ሲሆን ይህም በአንጻራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ በመሆኑ ኩራት ይሰማታል።
ባለሥልጣናት በአገሪቱ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር እንደዋለ ይናገራሉ። ነገር ግን አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሄዱ አሳሳቢ ሆኗል።
ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተጣሉ ገደቦችን ተከትሎ በየካቲት ወር አጋማሽ በቀን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 6000 ያህል ሆኗል።
መንግሥት በመጋቢት ወር ገደቦችን ማላላቱን ተከትሎ አዲስ የወረርሽኙ ማዕበል በቱርክ ተከስቷል።
በድጋሚ መንግሥት መጋቢት መጨረሻ ላይ ገደቦችን ለመጣል የተገደደ ሲሆን ይህ ግን ስርጭቱን ለመግታት በቂ አልሆነም።
በሚያዝያ ወር በቀን ከ 60,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ300 በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህ ለምን ተከሰተ?
መንግሥት ገደቦችን በፍጥነት ማንሳቱን እና የክትባቱ ሂደት መጓተቱን ተቺዎች እንደምክንያት ያቀርባሉ።
በ82 ሚሊዮን ሕዝብ ካላት ቱርክ እስካሁን የተከተቡት ከ22 ሚሊዮን ብዙም አልዘለለም።
ቱርክ በዋናነት የቻይናውን ሲኖቫክ ክትባት አነስተኛ ቁጥር ካለው የፋይዘር-ባዮንቴክ ጋር ለሕዝቧ አቅርባለች።
የጤና ሚኒስትሩ ፋህሬቲን ኮካ በቅርቡ "ለክትባቱ እንዲረዳን ሲኖቫክ፣ ፋይዘር-ባዮንቴክ እና የሩሲያውያን ስፑትኒክ 5ን ጨምሮ የክትባት ዲፕሎማሲን አፋጥነናል" ብለዋል።
ሌላው ትችት ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶጋን ላይ ያነጣጥራል። ማኅበራዊ ስብሰባዎች እና ሕዝባሰዊ ተቃውሞዎች ቢታገዱም ገዥው ኤኬ ፓርቲ በመጋቢት ወር በተሳታፊዎች የተሞሉ ስብሰባዎችን አካሂዷል።
ሳይንቲስቶች አዲሶቹ የቫይረሱ ዝርያዎች በተለይም የእንግሊዙ (ኬንት) ዝርያ የስርጭቱን ቁጥር ከፍ አድርጎታል ብለዋል።
የአዲሱ ስርጭት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ኤርዶጋን በመጨረሻም ከሐሙስ እስከ ግንቦት 17 ድረስ የሚዘልቅ ሙሉ እገዳ መጣሉን አስታውቀዋል።
አዲሶቹ እገዳዎች ምንድን ናቸው?
* ሰዎች አስፈላጊ ከሆኑ የግብይት ጉዞዎች እና ከአስቸኳይ ሕክምና ውጭ በቤት ውስጥ መቆየት አለባቸው
* በከተሞች መካከል የሚደረጉ ሁሉም ጉዞዎች ኦፊሴላዊ ማረጋገጫ ያስፈልጋቸዋል
* ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው ሲቆዩ በሕዝብ ማመላለሻ ተጠቃሚዎች ላይ የመጫን ገደቦች ይጣላሉ
* የአልኮሆል ሽያጭ ውስን ይሆናል
* አንዳንድ ሥራዎች ከአዲሱ ገደቦች ነጻ ተደርገዋል
ብዙ ባለሙያዎች አዲሱ እገዳ አስፈላጊ ነው በማለት ደስተኞች ሆነዋል።
አንዳንዶች ግን እገዳው ስርጭቱን በበቂ ሁኔታ ለመግታት ረጅም ጊዜ መቆየት እና በፈጣን የክትባት መርሃ ግብር ካልተደገፈ ውጤታማ ላይሆን ይችላል ብለው ይከራከራሉ።
ማንኛውም እርምጃ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ድጋፍም መስጠትን ማካተት አለበት ብለው ያምናሉ።
በመላው የቱርክ ኅብረተሰብ ዘንድ የቫይረሱን ከፍተኛ ስርጭት ለመግታት ቁርጠኝነት ሲኖር መንግሥትም ግልጽ እቅድ አስቀምጧል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን "አውሮፓ የእገዳ ማላላት ውስጥ እየገባች ነው። በዚህ ወቅት እኛን በቀን የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ወደ 5,000 መቀነስ እና ወደ ኋላ መቅረት የለብንም" ብለዋል።
እገዳዎቹ በቀሪው የረመዳን እና ከዚያ በኋላ ባለው የኢድ በዓላት ወቅት ተግባራዊ ሆነው ይቀጥላሉ።
ባለፈው ዓመት በቱርክ የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር 70 በመቶ ቀንሶባታል። እገዳው ለበጋ የጉብኝት ወቅት በጊዜ እንዲከፈት ይረዳል ብለው የቱሪስት ኢንዱስትሪው ባለድርሻዎች ተስፋ አድርገዋል።












