ኮቪድ-19፡ ቤት የመቀመጥ ገደብ ጉግልን ትርፋማ አድርጓል ተባለ

የጉግልና አልፋቤት መለያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የተጣለው ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደብ ለጉግል ትርፋማነት አስተዋጽኦ አድርጓል ተባለ።

የጉግል ባለቤት ድርጅት የሆነው አልፋቤት ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 17 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ያገኘ ሲሆን ይህም የ162 በመቶ ጭማሪ መሆኑ ተገልጿል።

ለትርፋማነቱም ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ እንቅስቃሴያቸው ሲገደብ የጉግልን አገልግሎቶች መጠቀማቸው በምክንያትነት ተቀምጧል።

ያለፉት ሦስት ወራትም በድርጅቱ ታሪክ ከፍተኛ ትርፍ የተመዘገበበት ነው ተብሏል።

ጉግል ይህን የትርፍ መጨመር "ደንበኞቼ ኢንተርኔት በመጠቀም የሚያከናውኗቸው ተግባራቶች መጨመር ያመጣው ነው" ሲል ገልጾታል።

"ባለፈው ዓመት ሰዎች የጉግል መፈለጊያን ተጠቅመው ራሳቸውን ከመረጃ ላለማራቅ፣ ለመዝናናት እና ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማስቀጠል ሲጠቀሙት ቆይተዋል" ሲሉ የአልፋቤት እና ጉግል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሱንዳር ፒቻዪ ገልጸዋል።

የዘርፉ ተንታኞችም የተዘጉ ኢኮኖሚዎች ሲከፈቱ እና የኢንተርኔት ላይ ማስታወቂያዎችም እየተበራከቱ ሲሄዱ ጉግል ከፍተኛ ትርፍ መሰብሰቡን ይቀጥላል ብለዋል።

ጉግል ባለፈው ሦስት ወራት በአጠቃላይ ከመፈለጊያ ንግዱ [Search business] የሰበሰበውን ገቢ በ30 በመቶ በመጨመር ወደ 31 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። ዩትዩብ ደግሞ በስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ የ49 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በሃርግሬቭስ ላንሱንግ የፍትሐዊነት ተንታኝ የሆኑት ሶፊ ሉንድ-ያትስ በበኩላቸው አልፋቤት "ጉግል በወረርሽኙ ሳቢያ በተገኘው ገቢ ልክ በክሬም ላይ እደተወረወረች ትልቅ ድመት ሆኗል" ሲሉ ትርፉን ገልጸውታል።

የቴክኖሎጂ ግዙፉ ኩባንያ ጉግል፤ ባልተለመደ መልኩ የማስታወቂያ ንግድ ድርጅት ወደመሆን ማዘንበሉንም ተንታኙ ተናግረዋል።

"የኮሮናቫይረስ ሲከሰት በተለይም የኢንተርኔት ላይ ግብይት በመጧጧፉ ምክንያት የአልፋቤት የንግድ ተቋማት ለእነዚህ ሸቀጦች ማስታወቂያ ማስነገራቸው ገቢያቸው እንዲተኮስ ምክንያት ሆኗል" ሲሉም ለከፍተኛ ትርፍ ያበቃውን ምክንያት አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ጉግል ከተለያዩ ተቆጣጣሪ ተቋማት በተለይም ፍትሐዊ የንግድ ውድድርን እና የግል ምስጢር መጠበቅን በተመለከተ እያጋጠመው ያሉት ጥያቄዎች ዋና ተግዳሮቶቹ ሆነው ቀጥለዋል።