ሳሚያ ሱሉሁ ሐሳን ቃለ መሃላ ፈጽመው የታንዛኒያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሆኑ

ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን

ሳሚያ ሱሉሁ ሐሳን ቃለ መሃላ ፈጽመው ሥልጣን በመረከብ የመጀመሪያዋ የታንዛኒያ ሴት ፕሬዝዳንት ለመሆን በቁ።

ሳሚያ የፕሬዝዳንትነት መንበሩን የተረከቡት ዳሬ ሰላም በሚገኘው ቤተ መንግሥት ውስጥ በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኃላፊ ኢብራሂም ጁማ አማካይነት በፈጸሙት ቃለ መሃላ ነው።

ፕሬዝዳንት ሳሚያ ወደዚህ ሥልጣን የመጡት ቀዳሚው ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ በልብ ችግር ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ነው።

የአገሪቱ ስድስተኛ ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቁት ፕሬዝዳንት ሳሚያ 61 ዓመታቸው ሲሆን ላለፉት አምሰት ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።

በታንዛኒያ ሕገ መንግሥት መሠረት አዲሷ ፕሬዝዳንት ለቀጣኦቾ አምስት ዓመታት በመሪነት አገሪቱን ያስተዳድራሉ።

ፕሬዝዳንት ሳሊሃ ረቡዕ ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የተነገረውን የታንዛንያ የፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊን ቦታ እንደሚተኩ ሲተበቅ ነበር።

ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ሁለተኛውን የአምስት ዓመት የስልጣን ዘመናቸውን በዚህ ዓመት የጀመሩ ሲሆን በድንገት በማለፋቸው ምክትል ፕሬዝዳንቷ ቀሪውን ጊዜ በመሪነት ያገለግላሉ ተብሏል።

ይህም ለምሥራቅ አፍሪካዋ አገር ስድስተኛና የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲያደርጋቸው፤ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር ከሆነችው የዛንዚባር ደሴቶች የመጡ ሁለተኛ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።

ሳሚያ የታንዛኒያን ፕሬዝዳንትንት መንበር ለመረከብ የሚያስችላቸውን ቃለ መሀላ ከፈጸሙ በኋላ እርሳቸው ይዘውት የነበረውን የምክትል ፕሬዝዳንትንት ቦታ የሚይዝ ዕጩ ለመሰየም ከፓርቲያቸው አመራሮች ጋር ይመክራሉ ተብሏል።

በታንዛኒያ ሕገ መንግሥት መሠረት ሳሚያ የዛንዚባር ደሴት ተወካይ በመሆናቸው ምክትላቸው ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል የሚወከሉ ይሆናሉ።

ለምክትልነት የሚሰየሙት ዕጩ ከአገሪቱ ፓርላማ አባላት የ50 በመቶውን ይሁንታ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

በአገሪቱ ሕግ መሠረት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን ሦስትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ዓመታት በፕሬዝዳንትንት ከቆዩ በቀጣይ ዙር በሚኖር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አንድ ጊዜ ብቻ እንዲወዳደሩ ይፈቀድላቸዋል።

ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን በፖለቲካው መድረክ ላይ ትኩረትን ያገኙት በ2014 (እአአ) አዲሱ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ረቂቅ ሲዘጋጅ የጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ሲሾሙ ነበር።

ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ የገዢው የሲ ሲ ኤም ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ተወዳዳሪ የነበሩት የጆን ማጉፉሊ ምክትል በመሆን በዕጩነት ቀረቡ።

በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ወቅት አብረዋቸው ሲጓዙ የነበሩትን የሙዚቀኛ ቡድን አባላትን 'ማማ' ወይም 'እናታችን' ብለው እንዲጠሯቸው መጠየቃቸውን ተዘግቧል።

አብረዋቸው የሠሩ ፖለቲከኞች እንደሚናገሩት ግለሰቧ የታንዛኒያ ዜጎች የማየት ዕድል ያላገኙት የመሪነት አቅም እንዳላቸው ይመሰክራሉ።

"የተለመደ ፖለቲከኛ ዓይነት ትመስላለች፤ ነገር ግን እምቅ አቅሟ በጣም ትልቅ መሆኑን ከእርሷ ጋር በቅርበት በሰራሁበት ጊዜ ለመመልከት ችያለሁ" ሲሉ የሕግ ባለሙያው ጃንዋሪ ማክባም ለቢቢሲ ስዋሂሊ።

ሌሎች ደግሞ ደፋር እና የማይወላውሉ ፖለቲከኛ እንደሆኑ ይናገሩላቸዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት በዋና ከተማዋ ዶዶማ ከተፈፀመባቸው የግድያ ሙከራ የተረፉትን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱን ሆስፒታል ድረስ በመሄድ ጠይቀዋቸዋል።

ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ባለትዳር ሲሆኑ ከባለቤታቸው ሃፊድ አሚር አራት ልጆች አሏቸው።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ከ1993-1994* - ሲልቪ ኪኒጊ፤ ሚልቺር ንዳዳዬ ከተገደሉ በኋላ የብሩንዲ ባላደራ ፕሬዝዳንት ሆኑ

ከ2006-2018 - ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰን፤ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት

ከ2009 - ሮዝ ፍራንሲን ሮጎምቤ፤ የፕሬዝዳንት ኦማር ቦንጎ ሞትን ተከትሎ የጋቦን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆኑ

ከ2012 - ሞኒክ ኦህሳን ቤልፑ፤ ፕሬዝዳንት አንሩድ ጀግነት ሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የሞሪሼስ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆኑ

ከ2012-2014 - ጆይስ ባንዳ፤ ከፕሬዝዳንት ቢንጉዋ ሙታሪካ ሞት በኋላ የማላዊ ፕሬዝዳንት ሆኑ

ከ2014-2016 - ካትሪን ሳምባ ፓንዛ፤ በአገሪቱ ፓርላማ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የሽግግር ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከ2015-2018 - አሚናህ ጉሪብ ፋኪም፤ የሞሪሺስ ፓርላማ ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጣቸው

ከ2018- አስካሁን ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በኢትዮጵያ ፓርላማ ለፕሬዝዳንትነት የተሾሙ

* ሁሉም የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ነው

መስመር
የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊን ታንዛኒያውያን በምን ያስታውሷቸዋል?