ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ፡ በኮሮናቫይረስ ስለመያዛቸው ሲወራባቸው የነበሩት የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ መሞታቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ በ61 ዓመታቸው ማረፋቸውን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት አስታወቁ።
የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበው እንደተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ባጋጠማቸው የልብ ሕመም ምክንያት በዳሬ ሰላም ሆስፒታል ሲረዱ ቆይተው ሕይወታቸው አልፏል።
ማጉፉሊ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ከሕዝብ ዕይታ ርቀው የነበረ ሲሆን ጤናቸው በተመለከተ የተለያዩ አሉባልታዎች ሲሰሙ ነበር።
ባለፈው ሳምነት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ቢናገሩም ምንም የተረጋገጠ ነገር አልነበረም።
ማጉፉሊ ኮሮናቫይረስ መኖሩን ከማይቀበሉ የአፍሪካ መሪዎች መካከል ቀዳሚው የነበሩ ሲሆን፣ ተህዋሲውን ለመከላከል መፀለይ እንዲሁም የተለያዩ እጽዋትን አፍልቶ መታጠን መፍትሄ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ሐሰን የፕሬዝዳንቱን ሞት ሲናገሩ "ዛሬ ብልሁ የታንዛኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ . . .መሪያችንን ማጣታችንን ስናገር በእጅጉ እያዘንኩ ነው" ብለዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ አክለውም ለ14 ቀናት ብሔራዊ የሐዘን ቀናት በመላው አገሪቱ እንደሚሆን አውጀው በታንዛኒያ በሁሉም ስፍራ ሰንደቅ ዓላማዎች ዝቅ ብሎ ይውለበለባሉ ብለዋል።
በታንዛኒያ ሕገመንግሥት መሰረት፣ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ሐሰን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ።
ማጉፉሊ በድጋሚ ተመርጠው የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት በዚህ ዓመት ነው።
ማጉፉሊ ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝብ የታዩት የካቲት 20/2013 ዓ.ም የነበረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃሲም ማጃሊዋ ከቀናት በፊት ፕሬዝዳንቱ "ጤናማ እና ጠንክረው እየሰሩ ናቸው" በማለት ተናግረው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ታመዋል የሚሉትንም በባሕር ማዶ የሚኖሩ ታንዛኒያውያንን "በጥላቻ የተሞሉ ናቸው" ሲሉ ገልፀዋቸዋል።
ነገር ግን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት ቱንዱ ሊሱ ምንጮቻቸው ማጉፉሊ በኮሮናቫይረስ ታመው በኬንያ ሕክምና እያገኙ መሆኑን አንደነገሯቸው ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
ማጉፉሊ ታንዛኒያ "ከኮቪድ-19 ነጻ" መሆኗን ባለፈው ሰኔ ወር ናይ አውጀው ነበር። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ውጤታማነት ላይ የተዘባበቱት ማጉፉሊ፣ በምርመራው ላይ ያላቸውን ጥያቄ፣ እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰዱ ጎረቤት አገራትን ይተቹ ነበር።
ታንዛኒያ በአገሪቱ ስላለው የኮሮናቫይረስ ሁኔታ ካለፈው ዓመት ግንቦት ጀምሮ ይፋ አድርጋ አታውቅም።
የታንዛኒያ መንግሥትም የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለመግዛት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
ሰኞ ዕለት የአገሪቱ ፖሊስ ስለፕሬዝዳንቱ ጤንነት የተዛባ መረጃ አሰራጭተዋል ያላቸውን ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን መግለፁ ይታወሳል።
ጆን ማጉፉሊ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት በ56 ዓመታቸው እኤአ በ2015 ነበር።
ምንም እንኳ አጨቃጫቂ የነበረ ቢሆንም በዚህ ዓመት በተካሄደ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠዋል።
ማጉፉሊ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በፀረ ሙስና ዘመቻቸው የሚታወቁ ቢሆንም፤ ተቃዋሚዎቻቸውን በማፈንና የተወሰኑ ነጻነቶች ላይ ገደብ በመጣል ይወቀሳሉ።
ነገር ግን ተቺዎቻቸው ሳይቀሩ ማጉፉሊ ለታንዛኒያ እድገት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ይመሰክራሉ። ታንዛኒያን ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያገናኙ ትልልቅ የባቡር መስመር ዝርጋታዎችን እንዲሁም በንግድ ከተማዋ ዳሬ ሰላም ባስጀመሩት የትራንስፖርት አገልግሎትን ስማቸው በበጎ ይነሳል።
ማጉፉሊ የአገሪቱ የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት መጠን ከፍ እንዲልና የፈረቃ ሥርዓት እንዲቀንስ በማድረግም ይመሰገናሉ።
በሥልጣን ዘመናቸው የታሪክ መዝገብ ላይ ጥቁር ነጥቡን የጣለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የያዙበት መንገድ ነው።
በታኒዛንያ በጣም ውሱን የሆነ የኮቪድ-19 ምርመራ ያለ ሲሆን እስካሁን ድረስ ስለመከላከያ ክትባቱ ምንም የተባለ ነገር የለም።
















