የመጭበርበር ጥያቄ በተነሳበት የታንዛንያ ምርጫ ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ በከፍተኛ ድምፅ አሸነፉ

የሲሲኤም ፓርቲ ደጋፊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተቃዋሚዎች ተጭበርበሯል ሲሉ በገለፁት ምርጫ የታንዛንያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ በሰፊ ደምጽ በድጋሚ አሸንፈዋል ፡፡

የማጉፉሊ ዋነኛ ተቀናቃኝ ቱንዱ ሊሱ በረቡዕ ምርጫ የፓርቲያቸው ወኪሎች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ስለምርጫው መጭበርበር የተነሱ ጥያቄዎችን ውድቅ አደርጓል፡፡

ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው በምርጫው ፕሬዚዳንቱ 84 በመቶ ድምጽ ሲያገኙ ሊሱ ደግሞ 13 በመቶ ደምጽ አግኝተዋል፡፡

አርብ ዕለት የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ የታዛቢ ልዑክ ምርጫውን "ሥርዓቱን ጠብቆ የተካሄደ" ሲል ገልጾታል፡፡

የቻዴማው ዕጩ የነበሩት ቱንዱሊሱ ባለፈው ሐሙስ ውጤቱን እንደማይቀበሉ ገልጸዋል። ምርጫው "በታንዛንያም ሆነ በዓለም አቀፍ ህጎች መሠረት የተካሄደ አይደለም፡፡ አንዳንዶች የመንግሥትን ሃብት ያለአግባብ በመጠቀም ስልጣን ላይ ለመቆየት ያደረጉት ሂደት ነው" ሲሉ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።

ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዳሬሰላም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ "ህገ-ወጥነት እና ከፍተኛ የድምፅ ልዩነት መኖሩ በውጤቱ ተዓማኒነት ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ይፈጥራሉ። ... የታንዛንያ መንግስት ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ያለው ቁርጠኝነትም ያሳስባል" ብሏል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ሴሚስቶክልስ ካይጃጌ በበኩላቸው በሐሰተኛ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ የቀረቡት ክሶች ማስረጃ ያለቀረበባቸው ናቸው ብለዋል፡፡

በታንዛንያ ምርጫ ከመሳተፋቸውም በተጨማሪ ከፊል ራስ ገዝ በሆነችው በዛንዚባር ደሴት ላይ ያሉ ነዋሪዎችም የራሳቸውን ፕሬዝዳንት መርጠዋል።

የሲሲኤም ዕጩው ሁሴን ምዊኒ ደግሞ 76 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል ፡፡

ተቀናቃኛቸው እና የኤሲቲ-ዋዛሌንዶው ዕጩ ማሊም ሴይፍ ሸሪፍ 19 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል። ደምጹ እስካሁን ከተሳተፉበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ትልቁ ሽንፈታቸው ሆኖ ተመዝግቧል።

ሐሙስ ዕለት ሴይፍ ሸሪፍ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ህዝባዊ ተቃውሞ ከጠሩ በኋላ በቁጥጥር ስር ወለዋል። በኋላም በዋስ ተለቀቅዋል፡፡