ተቃዋሚዎች አንሳተፍም ያሉበት የአይቮሪ ኮስት ምርጫ ተጀምሯል

የፎቶው ባለመብት, EPA
አይቮሪ ኮስት አወዛጋቢ የተባለውን ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ጣቢያዎቿን ልትከፍት ነው።
አገሪቱን በመምራት ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት አላሳን ኦታራን ሊተኩ ይችላሉ የተባሉት ግለሰብ በድንገት መሞታቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ በድጋሚ ለሶስተኛ ጊዜ እወዳደራለሁ በማለታቸው ነሐሴ ላይ በተቀሰቀሰ አመፅ ቢያንስ 14 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኦታራ ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደራቸው ህገ-ወጥ መሆኑን ዋነኞቹ የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች ፓስካል አፊ ንጉዬሳን እና ሄንሪ ኮናን ቤዲ ገልጸዋል፡፡
እንደማይመርጡ እና ህዝባዊ የእምቢተኝነት ጥሪም አስተላልፈዋል ፡፡
በአይቮሪ ኮስት ሕገ መንግስት መሠረት አንድ ፕሬዝዳንት ለሁለት ጊዜ ብቻ ስልጣን ላይ ይቆያል፡፡ ሁለት ጊዜ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ኦታራ ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ተናግረው ነበር፡፡
የገዢው ፓርቲ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር አማዱ ጎን ኩሊባሊ ባለፈው ሐምሌ በልብ ህመም ህይወታቸው አልፏል።
ይህን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ኦታራ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል ፡፡
ደጋፊዎቻቸው ህገ-መንግስቱ በ2016 በመሻሻሉ የመጀመሪያው የስልጣን ጊዜው አይቆጠርም ብለው ይከራከራሉ፡፡
ይህን ግን ተቃዋሚዎቻቸው አይጋሩትም። ይልቁንም ኦታራ ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደራቸው ሕገወጥ ነው ይላሉ፡፡
በአንዳንድ የአገሪቱ የፖለቲካ ሰዎች መካከል ለአስርት ዓመታት የዘለቀ ቁርሾ አለ፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሎረን ባግቦ እ.ኤ.አ. በ2010 የተካሄደውን ምርጫ በኦታራ መሸነፋቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የእርስ በእርስ ጦርነት ተነሳ።
ለአምስት ወር በዘለቀው ሁከት ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ባግቦ በዘንድሮው ምርጫ ለመወዳደር ቢፈልጉም በአይቮሪኮስት ፍርድ ቤት ጥፋተኛ መባላቸውን ምክንያት በማድረግ የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽኑ አግዷቸዋል፡፡
በኮሚሽኑ ካገዳቸው ወደ 40 የሚጠጉ ዕጩዎች መካከል አንዱም ሆነዋል።












