ቱርክና ግሪክ በከፍተኛ ርዕደ መሬት ተመቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቱርክና ግሪክ ክፉኛ በሚባል ርዕደ መሬት ተመቱ። ርዕደ መሬቱ የተከሰተው በቱርክ አጊያን የባህር ዳርቻ በኩልና፣ በሰሜናዊዋ የግሪኳ ሳሞስ ደሴት ነው ተብሏል።
በቱርኳ ኢዝሚር ግዛት 7 ሬክተር ስኬል የርዕደ መሬቱን መለካቱን የአሜሪካው የስነ ምድር ጥናት አስታውቋል።
ቱርክ በበኩሏ ርዕደ መሬቱ 6.6 ሬክተር ስኬል መሆኑን ያሳወቀች ሲሆን በዚህም አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 120 ሰዎችም ተጎድተዋል። በዚችው ግዛት 20 ህንፃዎች ፈራርሰዋል።
ርዕደ መሬቱ በተወሰነ መልኩ ጎርፍና የሱናሚ አውሎ ንፋስንም አስከትሎ ኢዝሚርና ሳሞስ ደሴትን አጥለቅልቋቸዋል።
ርዕደ መሬቱ በከተሞቹ መዲኖች አቴንስና ኢስታንቡል ድረስ የዘለቀ ሲሆን ጥልቁቱም 10ኪሎሜትር ነው ተብሏል። ቱርክ በበኩሏ ወደታች 16 ኪሎሜትር የዘለቀ ነው ብላለች።
ለርዕደ መሬት ተጋላጭ በሆኑት ቱርክና ግሪክ በርካታ ጊዜ የሚያጋጥም የተፈጥሮ ክስተት ነው።
በቱርኳ ሶስተኛ ታላቅ ከተማ ኢዝሚር በተፈጠረውም ርዕደ መሬት በርካቶች ደንግጠው በጎዳናዎች ላይ ሲሮጡ ታይተዋል።
በርካታ ፎቆች ያሉት ህንፃም ተደረማምሶ ሲፈርስ የሚያሳይ ቪዲዮም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መውጣቱን የቢቢሲ ጋዜጠኛ ኦርላ ጉሪን ከቤይሩት ዘግባለች።
በሌላኛው ቪዲዮ ላይ ደግሞ የከተማይቱ ነዋሪ ዘመድ ወዳጆቻቸውን በፍርስራሾች ውስጥ ሲፈልጉ ያሳያል።
ከዚህም በተጨማሪ ርዕደ መሬቱ ባስከተለው ጎርፍ የተነሳ ባህሩ ከፍ በማለቱም አሳ አጥማጆች በባህር መጥፋታቸው ተነግሯል።
በግሪክ ሱናሚ ባስከተለው ጎርፍ በሳሞስ ደሴት የሚገኙ በርካታ ህንፃዎች ፈርሰዋል ወይም ለጉዳት ተደርገዋል።
የደሴቲቷ ነዋሪዎች ከባህር ዳርቻዎች ራቅ እንዲሉም ተነግሯቸው ነበር።
በዛሬው እለት የተከሰተው ርዕደ መሬት በሌላኛው የግሪክ ደሴት ክሬት ደርሷል ተብሏል።
በተደረማመሱና በፈራረሱ ህንፃዎችም ውስጥ የጠፉ ሰዎችን ሲፈልጉ የሚያሳዩ ቪዲየዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ወጥተዋል።
በጥር ወርም በቱርኳ ምስራቃዊ ግዛት ኤላዚግ በደረሰ ርዕደ መሬት 30 ሰዎች ሲሞቱ 1 ሺህ 600 ተጎድተዋል።
በ2019 የግሪኳ መዲና አቴንስ በደረሰ ርዕደ መሬት ከተማይቷ ተናውጣ ነበር።
በ1999 በቱርኳ ኢዝሚት በደረሰው ርዕደ መሬት 17 ሺህ ሰዎች ሞተዋል።












