በሞዛምቢክ ህጻናት አንገታቸውን እየተቀሉ መሆናቸውን ሴቭ ዘ ችልድረን ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Rui Mutemba/Save the Children
በሞዛምቢክ ካቦ ዴልጋዶ አውራጃ የ 11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት ጭምር አንገታቸውን እየተቀላ ነው ሲል ሴቭ ዘ ችልድረን ገለጸ።
አንዲት እናት ከሌሎቹ ልጆቿ ጋር በተደበቀችበት የ 12 ዓመቱን ልጇ በተመሳሳይ መንገድ ሲገደል ማየቷን ለሴቭ ዘ ችልድረን ገልጻለች።
የሽምቅ ጥቃቱ ከተጀመረበት ከጎርጎሮሳዊያኑ 2017 አንስቶ ከ 2500 በላይ ሰዎች ሲገደሉ 700 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡
ከእስላማዊ መንግስት (አይ ኤስ) ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በአካባቢው ለተፈጠረው ግጭት ምክንያት ናቸው፡፡
ሴቭ ዘ ችልድረን በሪፖርቱ ከጥቃቱ በስተጀርባ ማን እንዳለ አልገለጸም። ሆኖም ከታንዛኒያ ጋር በሚያዋስነው እና በጋዝ በበለፀገው በሰሜናዊ የአገሪቱ አውራጃ አሰቃቂ ትዕይንቶችን ተፈናቃዮች መመልከታቸውን ገልጿል፡፡
ለደህንነቷ ሲባል ስሟ ያልተጠቀሰው አንዲት እናት እርሷ እና ሌሎች ልጆቿ በተደበቁበት የትልቅ ልጇ አንገት ሲቀላ መመልከቷን ትናገራለች፡፡
"በዚያች ሌሊት መንደራችን ጥቃት ደርሶበት ቤቶችም ተቃጥለዋል" ብላለች፡፡
"ጥቃቱ ሲጀመር ከአራቱ ልጆቼ ጋር ቤት ነበርኩ። ወደ ጫካ ለማምለጥ ስንሞክር የበኩር ልጄን ወስደው አንገቱን ቀሉት። እኛም እንዳንገደል በመፍራት ምንም ማድረግ አልቻልንም" ስትል ገልጻለች።
ሌላኛው እናት ደግሞ ልጇ በታጣቂዎቹ ሲገደል እርሷ እና ሌሎች ሦስት ልጆቿ ደግሞ ለመሸሽ መገደዳቸውን ተናግራለች፡፡
"የ 11 ዓመቱ ልጄ ከተገደለ በኋላ በመንደራችን መቆየቱ ስጋት ፈጥሮብናል" ብላለች፡፡
"ሌላ መንደር ወደ ሚገኘው የአባቴ ቤት ብንሄድም ከቀናት በኋላ ጥቃቶቹም እዚያም ቀጠሉ" ስትል ገልጻለች፡፡
በሴቭ ዘ ቺልድረን የሞዛምቢክ ዳይሬክተር የሆኑት ቻንስ ብሪግስ በበኩላቸው በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች "ከፍተኛ ህመም ፈጥሮብናል" ብለዋል፡፡
"ሠራተኞቻችን በመጠለያ ጣቢያዎች የሚነገራቸውን የመከራ ታሪኮች ሲሰሙ በእንባ ታጥበዋል" ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ የታጣቂዎቹን ድርጊት "ቃላት ከሚገልጹት በላይ ጭካኔ የተሞላበት" ሲል ገልጾታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ታጣቂዎቹ እነማን ናቸው?
ታጣቂዎቹ በአካባቢው አል-ሸባብ በመባል የሚታወቁ ሲሆን የአረብኛ ትርጉሙም ወጣቶች ማለት ነው፡፡ ይህም አብዛኛዎቹ ሙስሊም በሆኑባት ካቦ ዴልጋዶ ከሚኖሩ ሥራ አጥ ወጣቶች ድጋፍ እንደሚያገኝ ያሳያል፡፡
ተመሳሳይ ስም ያለው ቡድን በሶማሊያ ከአስር ዓመታት በላይ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ የሶማሊያው ቡድን አጋርነቱን ለአልቃይዳ ሲሰጥ የሞዛምቢኩ ቡድን ለተቀናቃኙ አይ ኤስ መሆኑን ይናገራል።
አንዳንድ ተንታኞች የአማጽያኑ መሰረት በማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ቅሬታዎች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያምናሉ። ብዙዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ከክልሉ ሩቢ (እንደ አልማዝ ያለ የከበረ ድንጋይ ነው) እና ጋዝ ያገኙት ጥቅም አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት አንድ የታጣቂ መሪ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት "እኛ [ከተሞቹን] የምንይዘው መንግሥት ፍትሃዊ አለመሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ድሆችን እያዋረደ ትርፉን ለበላዮች ይሰጣል" ብለዋል፡፡
ግለሰቡ ስለ እስልምና ያወራ ሲሆን "እስላማዊ መንግሥት ስለመመስረት እንጂ ስለ ኢ-አማኝ መንግሥት" ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል። በሞዛምቢክ ጦር ይፈጸማሉ የተባሉ በደሎችንም በመጥቀስ መንግሥት "ኢ-ፍትሃዊ" ነው ሲል በተደጋጋሚ ያማርራል፡፡
ብሪግስ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ እንደገለጹት ማኒፌስቶ ስለሌላቸው ትክክለኛ መነሻቸውን ማወቅ ከባድ ነው፡፡
"ወጣቶችን ለውትድርና እንዲቀላቀሏቸው ይጠየቁና አሻፈረኝ ካሉ ይገደላሉ። አንዳንድ ጊዜም አንገታቸውን ተቀልቶ ነው የሚገደሉት፡፡ በእውነቱ መጨረሻው ምን እንደሆነ መገመት ከባድ ነው" ብለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ጳጳስት ጉባኤ ልዑካን ቡድን ባለፈው ዓመት የካቦ ዴልጋዶ ዋና ከተማ የሆነችውን ፔምባን ከጎበኙ በኋላ "ሁሉም የብዙ አገራት ኮርፖሬሽኖች የክልሉን የማዕድንና የጋዝ ሃብቶች በመቆጣጠራቸው ጦርነቱ መጀመሩን ያናገርናቸው በሙሉ ተስማምተውበታል ማለት ይቻላል" ብለዋል፡፡
ካቦ ዴልጋዶ ምን ትመስላለች?
ካቦ ዴልጋዶ በሞዛምቢክ ካሉ እጅግ በጣም ድሃ አውራጃዎች አንዷ ስትሆን ከፍተኛ ያልተማሩ ሰዎች እና ሥራ አጥ ያለባት ናት፡፡
ከጎርጎሮሳዊያኑ 2009 እስከ 2010 ባለው ጊዜ ውስጥ በጣም ብዙ የሩቢ እና ግዙፍ የጋዝ ጉድጓዶች መገኘታቸው፣ የአካባቢው ሰዎች የሥራ ዕድል እና የተሻለ ህይወት እንደሚኖራቸው ገምተው ነበር። ነገር ግን እነዚህ ተስፋዎች ብዙም ሳይቆዩ በንነዋል፡፡
ሞዛምቢክ በ1975 ነፃነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ እያስተዳደራት የቆየው ፍሬሊሞ ፓርቲ አመራሮች እየተጠቀሙ ነው በሚል ቅሬታ ይቀርብባቸዋል፡፡
መንግሥት ዋና ትኩረቱ ወታደራዊ መፍትሄ መፈለግ ላይ ቢሆንም ሠራዊቱ ለመዋጋት በቂ አቅም የለውም፡፡
በመዲናዋ ማፑቶ የሚገኙት የአሜሪካ ኤምባሲ ባለሥልጣናት የአሜሪካ ወታደሮች ለሁለት ወራት ወታደሮችን በማሰልጠን "የሕክምናና የመገናኛ መሣሪያዎችን" እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
ለሞዛምቢክ ኃይሎች ስልጠና እንደሚሰጥ የአውሮፓ ህብረትም ባለፈው ዓመት አስታውቋል፡፡
ይህም ሞዛምቢክ ታጣቂዎችን ለመዋጋት እንዲረዷት የሩሲያ እና የደቡብ አፍሪካ ቅጥረኞችን መመልመሏን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ የሩሲያ ቅጥረኞች በአመጸኞቹ የደረሰባቸውን ኪሳራ ተከትሎ ከካቦ ዴልጋዶ መውጣታቸው ተገልጿል፡፡












