ኮሮናቫይረስ፡ ባይደን በመጪው ግንቦት ሁሉም አዋቂዎች ክትባት ያገኛሉ ባይ ናቸው

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሃገራቸው አሜሪካ በነሱ አቆጣጠር ሐምሌ 4 'ከኮቪድ-19 ነፃ የወጣችበት' ቀን ሆኖ እንዲከበር አቅደዋል።

መንበረ-ሥልጣን ከተረከቡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአሜሪካዊያን ንግግር ያደረጉት ባይደን ሁሉም ግዛቶች እስከ ግንቦት ድረስ አዋቂ ሰዎችን እንዲከትቡ አዛለሁ ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ውስጥ ክትባት ለማግኘት ዕድሜና የጤና ሁኔታ ግምት ውስጥ ይገባሉ።

ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተብሎ ከታወጀ አንድ ዓመት ሆኖታል። ግማሽ ሚሊዮን አሜሪካዊያን በወረርሽኙ አልቀዋል።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ሁሉም ስፖርታዊ ጨዋታዎች የታገቱበት ታዋቂው ተዋናይ ቶም ሃንክስ ኮቪድ-19 ያዘው ተብሎ አጀብ የተባለበት ወቅት ነበር።

አልፎም የያኔው ፕሬዝደንት ትራምፕ ከአውሮፓ ማንም ሰው እንዳይመጣብን ብለው ያወጁበት፤ ቢበዛ እስከ ፋሲካ ድረስ ብንቸገር ነው ቃል የገበቡት ወቅት ነበር ያለፈው ዓመት መጋቢት።

ለዜጎቻቸው ንግግር ያሰሙት ባይደን በአሜሪካ የነፃነት ቀን ሰዎች በትንሹም ቢሆን ሰብሰብ ብለው የሚያከብሩበት ቀን እንደሚሆን ተስፋ አድርገዋል።

"አንድ ላይ ከሆንን ጁላይ 4 [የአሜሪካ የነፃነት ቀን] ከወዳጅ ዘመዶቻችንና ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰብሰብ ብለን ስጋ እየጠበስን የነፃነት ቀን ከማክበር ማንም አያግደንም" ብለዋል ባይደን።

ፕሬዝደንቱ፤ አሜሪካዊያን የነፃነት ቀናቸውን "ከቫይረሱ ነፃ የሆኑበት" ቀን ሆኖ ይከበራል የሚል እምነት አላቸው።

በርካታ ሰዎች እንዲከተቡ በማሰብ የክትባት ጣቢያዎች እንዲስፋፉ እንዲሁም የእንስሳት ሐኪሞችና የጥርስ ሐኪሞች ክትባት መስጠት እንዲችሉ ይፈቀድላቸዋል።

ተንቀሳቃሽ የክትባት ጣቢያዎች ወደ መንደሮች ገብተው ክትባት ያልደረሳቸውን ይደርሳሉ ብለዋል ባይደን።

ባይደን በመጀመሪያዎቹ 100 የሥልጣን ቀናት ዕድሜያቸው 100 ሚሊዮን ሰዎች ለመከተብ ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን አሁን በ60 ቀናት ውስጥ ይህን ማሳካት እንደሚቻል እየተናገሩ ነው።

ምንም እንኳ መልካም ዜና ቢሰማም "ትግሉ ግን አልተቋጨም፤ አሁን የምንዘናጋበት ጊዜ አይደለም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

"ቫይረሱን ረትተን ወደ ተለመደው ተግባራችን ለመመለስ ሕብረት ያስፈልገናል።"

ኮሮናቫይረስ አሜሪካ የዘለቀው የዛሬ ዓመት ነበር። ነጋዴዎች ሱቃቸውን የዘጉቡት ተማሪና ሠራተኛ ውሎው ቤት የሆነበት ወቅት።

አሁን ግን የተስፋ ጭላንጭል እየታየ ነው ይላል ባለፈው ጦር መንበረ-ሥልጣኑን በምርጫ የተቆጣጠሩት ባይደን።

ከባይደን ንግግር ጎልቶ የወጣው ሁሉም አዋቂ ሰዎች በመጪው ግንቦት ወር መጀመሪያ ክትባት ይደርሳቸዋል ማለታቸው ነው።

በቅርቡ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ከግማሽ በላይ ሪፐብሊካኖች ለክትባት በጎ አመለካከት የላቸውም።

ይህ ጉዳይ ለባይደን ፈተና ሊሆን ይችላል የሚሉ በርካቶች ናቸው።

ባይደን ትላንት [ሐሙስ] በኮቪድ-19 ምክንያት ኪሳቸው ለተጎዳ አሜሪካዊያን የሚሆን 1.9 ትሪሊየን ዶላር ድጎማ አፅድቀዋል።

ብሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አሜሪካዊያን በነብስ ወከፍ 1400 ዶላር ሆኖ ይደርሳቸዋል።

በተጨማሪ 350 ቢሊዮን ዶላር ለግዛቶች ድጎማ፤ 130 ቢሊዮን ዶላር ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት እንዲሁም 49 ቢሊየን ዶላር ለኮቪድ-19 ምርምር፤ 14 ቢሊየን ዶላር ደግሞ ለክትባት ማስፋፊያ እንዲውል ፀድቋል።

ድጎማው በፕሬዝደንቱ ፊርማ ከመፅደቁ በፊት በአሜሪካ ኮንግረስ በኩል ሲያልፍ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ዴሞክራቶች በሙሉ ድምፅ ሲደግፉት አናሳዎቹ ሪፐብሊካኖች ደግሞ ተቃውመውታል።

አሜሪካ 29 ሚሊየን ዜጎቿ በኮቪድ-19 ተይዘዋል።