ታንዛኒያ የነፍሰጡር ሴቶችን ሽንት "ለመድኃኒትነት" በሚገዛ ኩባንያ ላይ ምርመራ ከፍቻለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, Pacific Press
የታንዛንያ የመድኃኒትና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣናት የነፍሰ ጡር ሴቶችን ሽንት መድኃኒት ለመስራት እየገዛ ያለ ኩባንያ ላይ ምርመራ መክፈታቸውን አስተወቁ።
የአገሪቱ ጋዜጣ 'ዘ ሲትዝን' እንደዘገበው ባለስልጣናቱ ምርመራ የከፈቱት ኩባንያው የበርካታ ነፍሰ ጡር ሴቶችን ሽንት ሰብስቧል የሚል ሪፖርት መድረሱን ተከትሎ ነው።
ይህ ኩባንያ ፖላይ (ቲዜድ) የሚል መጠሪያ እንዳለውና በአገሪቱም የመድኃኒትና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አለመመዝገቡን ባለስልጣናቱ ገልፀው ድርጅቱ እውቅና የለውም ብለዋል።
ኩባንያው ሽንቱን የሚሰበስበው በሚስጥር እንደሆነም እየተደረገ ያለው ምርመራ ማጋለጡን ዘ ሲትዝን በዘገባው አስነብቧል።
የምርመራው ሪፖርት እንደሚያሳየው አንድ የኩባንያው ሠራተኛ ከነፍሰ ጡር ሴቶች ሽንት እንደሚገዙ አምነዋል።
ሽንቱም ከመካንነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ለሚውል መድኃኒት ግብዓት ለማድረግ እንደሆነ ሠራተኛው ማስረዳታቸውን የምርመራው ሪፖርት አስፍሯል።
ሆኖም ሽንት መካንነትን ይቀርፋል የሚል ሳይንሳዊ መረጃ እንደሌለም ተጠቁሟል።
ሆኖም በርካታ ሰዎች ሽንትን ቆዳን ለማቅላት ከሚል በተጨማሪ መካንነትን ለመቅረፍ እንዲሁም ለሌሎች ጉዳዮች እንደሚጠቀሙበት መረጃዎች ያሳያሉ።
ባለስልጣናቱ እንዳሳወቁት ምርመራውን ካጠናቀቁ በኋላ አስፈላጊውን እርምጃ በኩባንያው ላይ እንወስዳለን ማለታቸው ተዘግቧል።












