ኢራናዊው የጁዶ ስፖርት ተወዳዳሪ በእስራኤል

ሳኢድ ሞላኤ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከእስራኤላዊ ተወዳዳሪ ጋር እንዳይፎካከር የተሰጠውን ትዕዛዝ ችላ ብሎ ከተወዳደረ በኋላ ወደ ኢራን ለመመለስ ፈቃደኛ ያልነበረው ኢራናዊው የጁዶ ተወዳዳሪ ለውድድር እስራኤል ገባ፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ 2019 በጃፓን በተካሄደው የጁዶ ዓለም ሻምፒዮና ላይ የተከሰተውን ትዕይንት ተከትሎ ሳኢድ ሞላኤ ለሕይወቴ እሰጋለሁ ማለቱ ይታወሳል።

ከክስተቱ በኋላ እስራኤልን እንደ ጠላት የምትቆጥረው ኢራን በዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን (አይ ጄ ኤፍ) ታገዳለች፡፡

ተወዳዳሪው በቴል አቪቭ ጨዋታዎች ላይ መገኘቱን "ታሪካዊ" ሲሉ የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ገልጸውታል፡፡

ሳኢድ በቴል አቪቭ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ውድድር ላይ ሞንጎሊያን ይወክላል፡፡

ሳኢድ እሁድ እስራኤል ደርሷል። በቶኪዮው ውድድር ኢራን ከእስራኤላዊው የጁዶ ተወዳዳሪ ሳጊ ሙኪ ጋር ነበር ሳኢድ እንዳይወዳደር ያገደችው። ሙኪ ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ተቃቅፈው ያሉበትን ፎቶ በማህበራዊ ድራምባዎች "እንኳን ደህና መጣህ ወንድም ዓለም" ከሚል መልዕክት ጋር አስፍሯል።

ሁለቱ ስፖርተኞች በቴል አቪቭ ጨዋታዎች ሊጋጠሙ የሚችሉበት ዕድል አለ።

"ይህ ለዓለም ትልቅ መልዕክት ነው፡፡ ይህ ኢራንን ወደ እስራኤል ይበልጥ ሊያቀርባት የሚችል ነገር ነው። ስፖርት በቀላሉ ሰዎችን እንዴት እንደሚያገናኝ እና ድንበር እንደሚሰብር ያሳያል" ሲል ሙኪ ለእስራኤል ራዲዮ ተናግሯል፡፡

የእስራኤል ስፖርት 1 ድረ-ገጽ ጉዳዩን "ታሪካዊ" ብሎ በመነሻ ገጹ አስፍሮታል። በእስራኤል በጣም ታዋቂ ከሆኑ የዜና አውታሮች አንዱ የሆነው ኔት ደግሞ ሳኢድን በቴላቪቭ ለመወዳደር በመወሰኑ "ደፋር" እና "ጀግና" ሲል ገልጾታል፡፡

የቶኪዮ ጨዋታዎች መጠናቀቅን ተከትሎ ጀርመን ያቀናው ኢራናዊው የጥገኝነት መብት የተሰጠው ሲሆን ከጎርጎሮሳዊያኑ መጋቢት 2020 ጀምሮ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሞንጎሊያን ወክሎ እንዲወዳደር ተፈቅዶለታል፡፡

ቀደም ሲል ወደ ኢራን ከተመለሰ "በቤተሰቦቼ እና በራሴ ላይ ምን ሊሆን ሳስብ እንደሚችል እፈራለሁ" ብሏል፡፡

ኢራን በቴል አቪቭ በሚካሄደው ውድድር መሳተፉን ለሚገልጸው ዜና በንቀት መልሳለች፡፡

"ይህ ክብር አይደለም። እስከመጨረሻው ከእርሱ ጋር የሚቆየው በግንባሩ ላይ የተጻፈ የውርደት እድፍ ነው። ምክንያቱም ጀርባውን ለትውልድ አገሩ እሳቤዎች ላይ አዙሯል " ብለዋል የኢራን የጁዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አራሽ ሚሬስማኤሊ፡፡

ኢራን የሳኢድን ውንጀላ "የሐሰት ጥያቄዎች" ናቸው ብላ በመጥቀስ ለዓለም አቀፉ የጁዶ ፌደሬሽን ይግባኝ ብላለች፡፡

የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የእስራኤልን ህልውና የማይቀበል ሲሆን እና ስፖርተኞቹም በዓለም አቀፍ ውድድሮች የእስራኤል ተፎካካሪዎቻቸውን እንዳይገጥሙ ታዘዋል፡፡