የኮሎምቢያ ሠራዊት ከ6 ሺህ በላይ ሰዎችን የአማፂያን አባል ናችሁ በሚል ገድሏል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሎምቢያ መከላከያ ኃይል እኤአ ከ2002 እስከ 2008 ባሉት ዓመታት ብቻ 6,402 ንፁኀን ዜጎችን የአማፂያን አባላት ናችሁ በሚል መግደሉን ይፋ ሆነ።
ይህ መረጃ የተሰማው በጦር ኃይሉ የተፈፀሙ ወንጀሎችን እየመረመረ በሚገኘው ልዩ ችሎት ነው።
በተጨማሪም የተፈፀሙት ግድያዎቹ ከዚህ በፊት ከተገመተው ሦስት ዕጥፍ እንደሚበልጡ ተገልጿል።
ምርመራው እየተደረገ ያለው በአገሪቱ በግራ ዘመም አማፂያን እና በጦር ኃይሉ መካከል ለዓመታት በነበረ ግጭት ወቅት የተፈፀሙ ወንጀሎችን ለማጣራት በተሰየመው ልዩ ችሎት ነው።
በ2016 በኮሎምቢያ መንግሥት እና በአማፂያኑ መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለአስርታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የነበረው ግጭት እንዲያበቃ አድርጓል።
የኮሎምቢያ ጦር ኃይል በወቅቱ ከዝቅተኛው የማኅበረሰብ ክፍል የተገኙ በርካታ ወጣቶችን የአማፂያኑ አባል ናችሁ በሚል ብቻ መግደሉ ይፋ ተደርጓል።
ጦሩ እነዚህን ወጣቶች ግራ ዘመም አማፂያን የሆኑት የኮሎምቢያ አብዮታዊ ታጣቂ ኃይሎች ቡድን አባል እንደሆኑ በማስመሰል ግድያውን የፈፀመ ሲሆን ይህም መንግሥት ታጣቂዎችን እያሸነፈ ነው የሚል ሐሰተኛ መረጃ ለመስጠት በማሰብ የተደረገ ነው ተብሏል።
ምርመራው እየተደረገ ያለው ለሰላም ልዩ ኃይል በተባለ ቡድን አማካኝነት ነው።
ይህ ቡድን ከአማፂያን ጋር መንግሥት በ2016 ከፈረመው የሰላም ስምምነት በኋላ የተቋቋመ ነው።
ይህ ቡድን በአማፂያኑም ሆነ በመንግሥት ታጣቂዎች የተፈፀሙ ጥቃቶችንና ግድያዎችን ያጣራል።
በዚህ የሰላም ልዩ ኃይል ፊት ቀርበው ጥፋታቸውን የሚያምኑ የእስር ጊዜ ይቀርላቸዋል የተባለ ሲሆን፣ ነገር ግን በእርቅ ስምምነቱ ላይ በሌላ በኩል አስተዋጽአ እንዲያደርጉ ይጠበቃል።
ይህም የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ አልያም የፈንጂ ማምከን ተግባር ላይ መሰማራት ሊሆን ይችላል።
ይህ ጊዜያዊ ችሎት በአማፂያኑ የተፈፀሙ እገታዎችን ካጣራ በኋላ ፊቱን የጦር ኃይሉ የአማፂያኑ አባላት ናቸው በሚል ሐሰተኛ መረጃ የገደላቸው ንፁኀን ዜጎችን ጉዳይ እየተከታተለ ነው።
የኮሎምቢያ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ለልዩ ችሎቱ ባለፈው ዓመት ባቀረበው ሪፖርት ላይ እኤአ ከ1988 እስከ 2014 ድረስ 2,249 ንፁኀን ዜጎች የአማፂያኑ አባላት ናችሁ ተብለው መገደላቸውን አምኗል።
ምርመራው እንደሚያሳየው ከሆነ ግን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህም በሦስት እጥፍ የላቀ ነው።
በተጨማሪም አብዛኞቹ ንፁኀን ዜጎች የተገደሉት ከ2002 እስከ 2008 ድረስ በፕሬዝዳንት አልቫሮ ኦሪቤ የስልጣን ዘመን ነው።
በሐሰተኛ መረጃ ንፁኀን ዜጎች የመገደላቸው ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው በ2008 ቢሆንም ይህ ድርጊትግን ከ1980 ጀምሮ ሲፈፀም እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
ከ1ሺህ 700 በላይ ሰዎችም በዚህ ወንጀል ላይ በመሳተፋቸው ብቻ በቁጥጥር ስር ውለው ታስረው ይገኛሉ።












