ቻይና ሃሰተኛ የኮቪድ-19 ክትባት ሲቸበችብ የነበረውን ግለሰብ አሠረች

ክትባት የሚከተብ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቻይና አንድ ንጥረ ነገር ከውሃ ጋር ደባልቆ የኮሮናቫይረስ ክትባት ነው በማለት ሲቸበችብ የነበረውን ቡድን መሪ በቁጥጥር ሥር አዋለች።

ቡድኑ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ፈሰስ አድርጎ ሃሰተኛ የኮቪድ-19 ክትባት አሽጎ ሲያጓጉዝ ነበር ተብሏል።

ኮንግ በሚል ስያሜው የሚታወቀው ግለሰብ ትክክለኛ የክትባት ብልቃጦችን አስመስሎ በመሥራት ከ58 ሺህ በላይ ክትባቶችን አምርቷል።

ክትባቶቹ ወደ ውጭ ሃገር ታሽገው እንደተላኩ ቢደረስበትም ወደ የትኛው ሃገር እንደተላኩ መረጃው የለም።

ኮንግ በተመሳሳይ ወንጀል በቁጥጥር ሥር ከዋሉ 70 ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው።

ቤይጂንግ ሃሰተኛ የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ገበያ ላይ እንደዋሉ ከደረሰችበት በኋላ ወንጀለኞቹን ለቅሞ ለማሰር ቃል ገብታ ነበር።

ምንም እንኳ ጉዳዩ አደባባይ መውጣት የጀመረው ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ቢሆንም ከሰሞኑ ግን አዳዲስ መረጃዎች ብቅ ማለት ጀምረዋል።

በማጭበርበር የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ጉዳይ ያየው ፍርድ ቤት ኮንግና አጋሮቹ 18 ሚሊዮን ዩዋን አትርፈዋል ብሏል።

ገንዘቡ ወደ ዶላር ሲመነዘር 2.7 ሚሊዮን ገደማ ይሆናል።

ግለሰቦች ከባለፈው ነሐሴ ጀምሮ ሳሊን ሶሉሽን የተሰኘ ንጥረ ነገር እንዲሁም ውሃ በሲሪንጅ ወደ ብልቃጡ በመሙላት ነው ሲያመርቱ የነበረው።

600 ብልቃጦች ወደ ውጭ ከመላካቸው በፊት ወደ ሆንግ ኮንግ ተጓጉዘው እንደነበርም ተደርሶበታል።

ብልቃጦች ለገበያ እየቀረቡ የነበረው ከትክክለኛ ክትባት አምራቾች 'በውስጥ መስመር' የተገኙ ናቸው በሚል መንገድ ነበር።

በሌላ መዝገብ ደግሞ ሃሰተኛ ክትባቶች በርካሽ ዋጋ ሆስፒታሎች ውስጥ ሲሸጡ እንደነበር ፍርድ ቤቱ ተመልክቷል።

የቻይና ከፍተኛው ችሎት ክልላዊ ወኪሎች ከፖሊስ ጋር ተባብረው ወንጀሎቹን ለሕግ እንዲያቀርቡ አሳስቧል።

የቻይና ባለሥልጣናት ከባለፈው ሳምንት በፊት 100 ሚሊዮን ሰዎች እንከትባለን ብለው አስበው የነበረ ቢሆንም እስካሁን 40 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ናቸው የተከተቡት።

ነገር ግን ቻይና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በቁጥጥር ሥር በማዋል ረገድ ከዓለም ሃገራት ቀድማ የምትጠቀስ ናት።