ዘብጥያ አልወርድም ያለው ራፐር ዩኒቨርስቲ ገብቶ መሸገ

የ33 ዓመቱ ፓብሎ ሃስል ከራፐርነቱ ባሳገር በፖለቲካዊ አቋሙ ጽንፈኛ ግራ ዘመም አመለካከት እንዳለው ይነገራል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የ33 ዓመቱ ፓብሎ ሃስል ከራፐርነቱ ባሳገር በፖለቲካዊ አቋሙ ጽንፈኛ ግራ ዘመም አመለካከት እንዳለው ይነገራል

ስፔናዊው ራፐር በትዊትር እና በግጥሞቹ የአገሪቱን ንጉሣዊ ሥርዓትና ፖሊስን በመዝለፉ የተጣለበትን ቅጣት በመሸሽ በዩኒቨርስቲ ውስጥ መመሸጉ ተገለፀ።

ራፐሩ ዘውዳዊ ሥርዓቱን በመዝለፍ እና የአገሪቱን ተቋማት በመዝለፍ እንዲሁም አሸባሪነትት አንቆለጳጵሶ በማቅረብ የዘጠኝ ወር እስር ተፈርዶበት ነበር።

ፓብሎ ሃስል እስከ ባለፈው ሳምንት አርብ ድረስ እጁን እንዲሰጥ ቢጠየቅም በትዊተር ሰሌዳው ላይ ባሰፈረው መልዕክት ከደጋፊዎቹ ጋር በመሆን በለለይዳ ዩኒቨርስቲ መመሸጉን አስታውቋል።

በትዊተር ሰሌዳው ላይ “እኔን ከዚህ ወስደው ለማሰር ሰብረው መግባት አለባቸው” ብሏል።

የአገሪቱ ፍርድ ቤት ፓብሎ ሃስልን በቁጥጥር ሥር እንዲውል የሰጠው ውሳኔ ተፈጻሚ ከሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋረ በተያያዘ ወደ ማረሚያ ቤት የገባ ዝነኛ ሰው ይሆናል።

በስፔን ዘውዳዊ ሥርዓትን ከመዝለፉ ባሻገር ሙዚቀኛው በትዊተር ላይ በሚጽፋቸው እንዲሁም በሙዚቃዎቹ ግጥሞች ውስጥ የአገሪቱ ፖሊስ፣ ተቃዋሚ ስፈኞችን እና ስደተኞችን በማሰቃየት እና በመግደል ወንጀል ይከስሳቸዋል።

ለለይዳ ዩኒቨርስቲ በካታሎናውያን ከተማ ለለይዳ ከተማ የምትገኝ ስትሆን ከባርሴሎና 150 ኪሎ ሜትር ትርቃለች።

ድምጻዊው በዩኒቨርስቲው ገብቶ የመሸገው ከ20 ደጋፊዎቹ ጋር እንደሆነ ታውቋል።

የእርሱን እስር በመቃወም ከ200 በላይ ታዋቂ የአገሪቱ የጥበብ ባለሙያዎች የድጋፍ ፊርማ አሰባስበዋል።

የስፔን መንግሥት በጥበብ ሥራዎች ውስጥ የሚነሱ የጥላቻ ንግግሮች፣ ሃይማኖትንና ዘውዳዊ ስርዓቱን መዝለፍ፣ ሽብርተኝነትን ማግነን ላይ የሚጣሉ ቅጣቶችን የመቀነስ እቅድ አለው።

ራፐር ፓብሎ ሃስል ትክክለኛ ስሙ ፓብሎ ሪቫዱላ ዱሮ ሲሆን የካታላናውያንን የመገንጠል ጥያቄ ይደግፋል።

እኤአ በ2017 የካታላን ተገንጣይ ቡድኖች ስፔን ውስጥ ትልቅ የፖለቲካ ቀውስ አስነስተው ነበር።

በስፔን ከዚህ በፊትም ጦማሪያን “ሽብርተኛነትን በማግነን” ወንጀል ተከስሰው ያውቃሉ።

በ2018 ሌላ ቫልቶኒክ በመባል የሚታወቅ ስፔናዊ ራፐር ለሶስት ዓመት ተኩል ታስሮ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ወደ ቤልጂየም ተሰድዷል።

ድምጻዊው አሁንም በስፔን መንግሥት ከሚፈለጉ ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ይገኛል።