“ጃኮብ ዙማ ፍርድ ቤትን በመናቅ ክስ ዘብጥያ ሊወርዱ ይገባል” የደቡብ አፍሪካ ዳኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ልዩ ፍርድ ቤት ዳኛ የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን ፍርድ ቤት ተዳፍረዋል ሲሉ ከሰሱ። በዚህም የእስር ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል ብለዋል።
የ79 ዓመቱ ጃኮብ ዙማ ፍርድ ቤት ተዳፍረዋል የተባሉት እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ፍርድ ቤት መገኘት ሲኖርባቸው በዚህ የኮሚሽኑ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ፍቃደኛነት ባለማሳየታቸው ነው።
ፍርድ ቤቱ እውነትን አፈላላጊ ኮሚሽን አቋቁሞ የዙማን ጉዳይ እየተመለከተ የነበረ ሲሆን ጃኮብ ዙማ ግን ዳኛ ሬይ ዞንዶ በሚመሩት የዚህን እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን የፍርድ ሂደት ላይ ሊገኙ አሻፈረኝ ብለዋል።
ዳኛው እንዳሉት የጃኮብ ዙማ ፍርድ ቤቱን የመናቅና የመድፈር ተግባር ሕግ አልባነትን የሚያበረታታ ነው። ዜጎችም በሕግ ሂደት እንዳያምኑ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ነው።በመሆኑም የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዙማን ፍርድ ቤትን በመዳፈር ክስ የእስር ቅጣት እንዲበይንባቸው እጠይቃለሁ ብለዋል።
ጃኮብ ዙማ በበኩላቸው የኮሚሽኑ ዳኛ ሬይ ዞነዶ ገለልተኛ አይደሉም እርሳቸው በሚያስችሉት ፍርድ ቤትም አልገኝም ብለዋል።
ከዚህ ቀደምም እኚህ የኮሚሽኑ ዳኛ ከቦታቸው እንዲለቁ ጃኮብ ዙማ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ዳኛ ዞንዶ ግን የዙማን ክስ ቸል ብለዋል። ሥራዬን ገለልተኛ ሆኜ የምሠራ ሰው ነኝ ሲሉም ተናግረዋል።
እስከ አሁን 40 የሚሆኑ ምስክሮች ዙማ ሙስኛ እንደነበሩ መስክረዋል።
ዙማ ከቀረበቡባቸው ክሶች መካከል ብልጹግ የሚባሉትን ቢሊየነሮቹን የጉብታ ቤተሰብ አባላት የደቡብ አፍሪካን ሀብት እንዲቀራመቱ አድርገዋል የሚሉ ይገኙበታል።
የጉብታ ቤተሰብ በደቡብ አፍሪካ ፖሊሲ እንዲቀየር፣ የካቢኔ አባላት ሹም ሽር እስከማድረግ ተጽእኖ ነበራቸው፤ ይህም የሆነው በዙማ ምክንያት ነው ተብሏል።
ጃኮብ ዙማም ሆኑ የጉብታ ቤተሰብ ክሱን ያስተባብላሉ።
የደቡብ አፍሪካ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ባለፈው ወር ጃኮብ ዙማ በዚህ የኮሚሽን ችሎት እንዲገኙ አዝዞ ነበር።
ሆኖም ትናንት ሰኞ ጃኮብ ዙማ በችሎት አለመገኘታቸውን ተከትሎ ዳኛ ሬይ ዞንዶ “ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው፣ ዙማ ግን ከዚህ አስተሳሰብ የሉበትም፤ ይህ ደግሞ ሕዝብ በሕግ የበላይነት እንዳያምን የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ጃኮብ ዙማ ፍርድ ቤቱን በመናቅና በመዳፈራቸው ከፍተኛው ፍርድ ቤት የእስር ቅጣት እንዲበይንባቸው ጠይቀዋል።
ዙማ ዳኛ ዞንዶ ይህን አስተያየት ከሰጡ በኋላ ያሉት ነገር የለም።
ሆኖም የዙማ ደጋፊዎች የወታደር የደንብ ልብስ ለብሰው የዙማ የትውልድ ስፍራ በመሄድ ባሳዩት ትእይንት የሚወዷቸውን ጃኮብ ዙማን እስከመጨረሻው እንደሚከላከሉ ቃል ገብተዋል።
ጃኮብ ዙማ ከሥልጣን በሕዝብ ግፊት እንዲለቁ የሆኑት በ2018 ሲሆን ይህም የቀረበባቸውን የሙስና ክስ ተከትሎ ነው።
ጃኮብ ዙማ 9 ዓመት ያህል በደቡብ አፍሪካ በሥልጣን ቆይተዋል።
ተተኪያቸው ሲሪል ራማፎሳ ወደ ሥልጣን የመጡት የሙስና መረቡን እበጣጥሳለሁ በሚል ቃል ገብተው ነበር።












