አዲሷ የዓለም ንግድ ድርጅት አለቃ ስለ ኮቪድ ክትባት ማስጠንቀቂያ ሰጡ

ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አዲሷ የዓለም ንግድ ድርጅት ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመፍታት ክትባትን መደበቅ መወገድ አለበት፡፡

ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ “የበለፀጉ አገራት ህዝባቸውን እየተከተቡ እና ድሃ አገራት መጠበቃቸው” መቆም አለበት ብለዋል፡፡

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በርካታ ሃገራት በድንበራቸው ውስጥ የሚሠሩ ክትባቶች ወደ ውጭ እንዳይላክ ለመከላከል ሞክረዋል፡፡

ዶ/ር ኦኮንጆ-ኢዊላ ክልከላው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን የመከላከል ሥራ እንደሚያደናቅፍ ተናግረዋል፡፡

“የበሽታው ወረርሽኝ ተፈጥሮ እና የተለያየ ዓይነት ዝርያዎች በመኖራቸው እያንዳንዱ ሀገር ህዝቡን በመከተብ የመከላከል እርምጃ እስካልወሰደ ድረስ ማንም ሀገር ደህንነት እንደማይሰማው ያደርገዋል” ብለዋል፡፡

የክትባት አለቃ

እስከ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ድረስ ዶ/ር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ በዓለም ዙሪያ የክትባት ተደራሽነትን ለማሳደግ ያለመው ዓለም አቀፍ የክትባት ጥምረትን (GAVI) ይመሩ ነበር። አሁን የዓለም ንግድ ድርጅት በዚህ ረገድ የሚከናወኑ ወሳኝ ሥራዎች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡

ብዙ መድሃኒት አምራቾችን በማበረታታት ክትባቱንማምረት እንዲቻል የዓለም ንግድ ድርጅት በአዕምሯዊ ንብረት ላይ ያለውን አቋም እንዲያለዝብ የሚጠይቁ ወገኖች አሉ። ዶ/ር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ “አንዳንድ ታዳጊ አገራት ነፃ እንዲሆኑላቸው ሲጠይቁ ያደጉ አገራት ግን ይህ በአዕምሯዊ ንብረት ላይ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ሲሉ ይሰማቸዋል” ብለዋል፡፡

እሳቸው ግን “ሦስተኛው አማራጭ ደግሞ የአዕምሯዊ ንብረት ጉዳዮች በአግባቡ መያዛቸውን እያረጋገጡ በቂ አቅርቦቶች እንዲኖሩ ለአምራቾች ፈቃድ መስጠት ይቻል” ይላሉ፡፡

የኦክስፎር ድአስትራዜኔካ ክትባት በሰጠው ፈቃድ ተጠቅሞ የህንዱ ሴረም ኢንስቲትዩት ክትባት እያመረተ መሆኑን በምሳሌነት ይነሳል፡፡

አዲሷን የዓለም ንግድ ድርጅት መሪን የሚገጥም እጅግ አንገብጋቢ ፈተና ወረርሽኙ ቢሆንም እሱ ብቻ ግን አይደለም፡፡

ህግጋቱ ጊዜ ያለፈባቸው እና ራሱንከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ለማላመድ ቀርፋፋ ነው ብለው በሚያምኑ በርካታ አገራት ዘንድ ድርጅቱ ጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት ትግል ላይ ይገኛል።

ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ድጋፍ ባለማግኘቱ ከተጓተተው የምርጫ ሂደት በኋላ ዶ/ር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ አዲሱ ኃላፊነት ምን እንደሆነ ያስታውሳሉ።

“የመጀመሪያዋ ሴት እና የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ በመሆኔ እኮራለሁ” ብለዋል፡፡

በዓለም ባንክ ኃላፊነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ በነበሩበት ወቅት ያገኙትን ዝና እንዲሁም የናይጄሪያ ፋይናንስ ሚኒስትር በመሆን ሃገራቸው ከዓለም አቀፍ ዕዳዎች ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ማድረጋቸውን ለመቀጠል ይፈልጋሉ፡፡

“የዓለም ንግድ ድርጅት ህጎችን በማዘመን የ 21 ኛው ክፍለዘመን እውነታዎችን በማሟላት በአባላቱ መካከል በተሰበረውን የመተማመን እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ብዙ መሠራት ያለበት ጉዳይ” አለ ይላሉ፡፡

የኮሮናቫይረስ ተግዳሮቶችን መቋቋም ከተቻለ እነዚያ “ትናንሽ ሂደቶች፣ ቀደምት ድሎች እና ስኬቶች መተማመንን ለመፍጠር እና ትልቁን ማሻሻያ እንዲደረግ ያስችላሉ” ብለዋል፡፡

የአሜሪካ-ቻይና የንግድ ጦርነት

የዓለም ንግድ ድርጅት የማስፈፀሚያ ስልቶች ስለሌሉት የአሜሪካ-ቻይና የንግድ ጦርነት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የታገለበት ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ግን የአሜሪካ ታሪፎች ከዓለም አቀፍ የንግድ ህጎች ጋር የማይጣጣሙ ናቸው የሚል ብይን ሰጥቷል፡፡

ዶ/ር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዊላ “እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አሜሪካም ሆነ ቻይና አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ለማድረግ በጣም አጋዥ ልንሆን እንችላለን” ብለዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት በብዙ መስኮች መሻሻል ለማምጣት የተቸገረበት አንዱ ምክንያት ውሳኔ የሚሰጠው በ164 አባል ሃገራቱ ውሳኔ በመሆኑ ነው፡፡

ውሳኔዎች በጋራ መግባባት ላይ ሳይሆን በአብላጫ ድምፅ መወሰን ይኖርባቸዋል ወይ ተብለው ለተጠየቁት ዶ/ር ኦኮንጆ-ኢዊላ “ይህ የውሳኔ አሰጣጥ ዘይቤ ፈጠራዎችን ወይም ለአባላቱ የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚያደናቅፍ መሆን የለበትም” ብለዋል፡፡