ኮካ-ኮላ ከወረቀት በተሠራ ኮዳ ብቅ ሊል ነው

ኮካ ኮላ የመጀመሪያውን ሙከራውን በሁለት ሺህ የወረቀት ቡትሌዎች ለመሞከር አቅዷል

የፎቶው ባለመብት, COCA-COLA

የምስሉ መግለጫ, ኮካ ኮላ የመጀመሪያውን ሙከራውን በሁለት ሺህ የወረቀት ቡትሌዎች ለመሞከር አቅዷል

ኮካ-ኮላ ምርቶቹን በፕላስቲክ ከማሸግ ለመቆጠብ ባቀደው መሠረት በወረቀት ኮዳዎች ብቅ ሊል መሆኑን አስታውቋል።

ፔፐር ቦትል በተባለው የዴንማርክ ኩባንያ የሚመረቱት የወረቀት ኮዳዎች ጠንከር ካለ ወረቀትና ከቀጭን ፕላስቲክ የሚሠሩ ናቸው።

ነገር ግን በጊዜ ሂደት ኩባንያው ሙሉ በሙሉ ከወረቀት በተሠራ ኮዳ ኮካ-ኮላ ለማከፋፈል አቅዷል።

አዲሱ ከወረቀት የሚሠራ ኮዳ ምንም ዓይነት ፋይበር ወደ ፈሳሹ እንዳይገባ ማድረግ አለበት።

ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን የኮካ-ኮላ ጣዕም ሊቀየር እንዲሁም ጤና ላይ አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል ተነግሯል።

ነገር ግን ታላላቅ ኩባንያዎች የኮካ-ኮላ ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው እያሉ ነው።

ኮካ በፈረንጆቹ 2030 ምንም ዓይነት ተረፈ ምርት የሌለው ምርት ለማምረት ቆርጦ ተነስቷል።

'ብሬክ ፍሪ ፍሮም ፕላስቲክ' የተሰኘ አንድ ኩባንያ ኮካ-ኮላ በዓለማችን በካይ ፕላስቲክ አምራች ኩባንያ ነው ሲል ባለፈው ዓመት ፈርጆት ነበር።

ፈተና የሚሆነው የወረቀት ኮዳው መሰል መጠጦች የሚፈጥሩትን ግፊት መቋቋም እንዲችል ማድረግ ነው።

እንደ ኮላና ቢራ ያሉ መጠጦች ግፊት ተጨምሮባቸው ስለሚታሸጉ የወረቀት ኮዳው ይህንን መቋቋም አለበት።

አልፎም የወረቀት ቡትሌው ኩባንያዎች በሚፈልጉት ልክና ቅርፅ ተጣጣፊ እንዲሆን ይጠበቅበታል።

የኩባንያዎቹ ስም የሚፃፍበት ቀለምም ወደ ውስጥ እንዳይሰርግ ሆኖ ሊሠራ ይገባዋል።

ኮዳ አምራቹ ኩባንያ ከሰባት ዓመታት ሙከራ በኋላ ይህን ወረቀት ማምረት ችያለሁ እያለ ነው።

የወረቀት ኮዳዎቹ በሚቀጥለው ክረምት ሃንጋሪ ውስጥ አዴዝ የተሰኘው የኮካ-ኮላ የፍራፍሬ መጠጥ ታሽጎባቸው ለገበያ ይቀርባሉ ተብሏል።

አብሱሉት የተሰኘው ቮድካ አምራች ኩባንያ 2 ሺህ የሚሆኑ በወረቀት ኮዳ የታሸጉ መጠጦችን አምርቶ ዩኬና ስዊድን ውስጥ ለገበያ ለማቅረብ ተሰናድቷል።

ቢራ አምራኡ ካርልስበርግ ደግሞ ለቢራዎቹ የሚሆኑ የወረቀት ኮዳዎችን ለማምረት ደፋ ቀና እያለ ነው።

ኮካ-ኮላ እንዲሁም አብሶሉት የተሰኙት ፋብሪካዎች በቅርቡ የሚያደርጓቸው ሙከራዎች በወረቀት የታሸጉ መጠጦች እንዴት ከቦታ ቦታ ሊጓጓዙ ይችላሉ የሚለውንም መለያ ናቸው።

ኮካ-ኮላ የወረቀት ኮዳዎቹ ከፈሳሹ ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ ሲል የኮዳዎቹን ውስጠኛ አካል ከእፅዋት በተሠራ ቁስ ሊለብጠው አስቧል።

ለጊዜው የወረቀት ኮዳዎቹ የፕላስቲክ ቆርኪ ቢኖራቸውም በጊዜ ሂደት ወደ ወረቀት ይቀየራሉ ተብሏል።