የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የፕላስቲክ ብክለትን ጨምሮታል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, SAS
የባህር ዳርቻዎችን የሚያጸዳ አንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅት እንዳስታወቀው ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽን በኋላ የፕላስቲክ ቆሻሻ ብክለት እንደ አዲስ በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል።
'ሰርፈርስ አጌኒስት ሲዌጅ' የተሰኘው ድርጅት እንደገለጸው ከወረርሽኙ በኋላ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችና ሌሎች የፕላስቲክ ምርቶች በባህር ዳርቻዎች አካባቢ በብዛት ተገኝተዋል።
ድርጅቱ አክሎም ሰዎች ወረርሽኙን እንደ ምክንያት በመጠቀም ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የተለያዩ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም የጀመሩ ሲሆን አወጋገድ ላይም ቢሆን ቸልተኝነት ተስተውሏል ብሏል።
ከፊታችን መስከረም ወር ጀምሮም እንዲህ አይነት ተግባር ሲፈጽሙ የሚገኙ ሰዎችንና ድርጅቶችን የመውቀስና የማሳፈር ቅስቀሳ በማህበራዊ ሚዲያ ለመጀመር ታስቧል።
ከባህር ዳርቻዎች በተጨማሪም በሀይቆችና ወንዞችም የፕላስቲክ ብክለት በስፋት እየታየ ነው። ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እንዲሁም ሌሎች የግል ንጽህና መጠበቂያዎችን ከተጠቀሙ በኋላ እንዴትና የት እንደሚያስወግዱ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ተጠቁሟል።
''የፕላስቲክ ጠርሙሶችና እቃ መያዣዎችን በውሃ አካባቢዎች ከዚህ በፊትም የተለመደ ነገር ቢሆንም ባለፉት ሶስትና አራት ወራት የተያው ግን ከምን ጊዜውም ቢሆን ከፍ ያለ ነው'' ብሏል ምግባረ ሰናይ ድርጅቱ።
በዚህ ምክንያትም ሰዎች በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስኮችን እንዲሁም ሌሎች መገልገያዎችን መጠቀም እንዲያዘወትሩ ምክር እየተሰጠ ነው።
ከአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች በተጨማሪ በውሀ አካባቢዎች ከተገኙት የፕላስቲክ ምርቶች መካከል የውሃ መጠጫዎች፣ ጓንቶች፣ የፕላስቲክ ማንኪያና ሹካዎች እንዲሁም ኮዳዎች ይገኙበታል።
በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኙ ባህር ዳርቻዎች በተደረገ ዳሰሳ እነዚህ የፕላስቲክ ምርቶች በብዛት ተስተውለዋል።
ምግባረ ሰናይ ድርጅቱም ይህንን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ 600 የሚደርሱ የባህር ባርቻና የወንዝ ዳር አጽጂዎችንለማሳተፍ ያሰበ ሲሆን የፕላስቲክ ምርቶቻቸው በብዛት የሚገኙ ድርጅቶችንም የማጋለጥና የማስተማር ዘመቻ ለማካሄድ አቅዷል።












