ፌስቡክና ትዊተር "የሩስያን መረብ በጣጠስን" አሉ

የትዊተርና ፌስቡክ ኣርማዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፌስቡክ አነስተኛ የትስስር መረብ ያላቸውንና የሩስያ እጅ አለበት ያላቸውን አካውንቶችና ገፆች መዝጋቱን አስታወቀ።

ኩባንያው እነዚህ ገፆች የከፈቱት ዘመቻ በቀጥታ የሚገናኘው እኤአ በ2016 የአሜሪካ ምርጫ ላይ ጣልቃ ገብቷል ተብሎ የሚወነጀለውና ከሩስያ መንግሥት ጋር ቅርብ የሆነው የሩሲያ ኢንተርኔት ምርምር ኤጀንስ (IRA) ጋር ነው ብሏል።

ትዊተርም በበኩሉ ከዚሁ ድርጅት ጋር ግንኙነት ያላቸው አምስት አካውንቶችን መዝጋቱን ገልጿል።

ድርጅቱ ስራውን ያከናውን የነበረው መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ስም ተመዝግቦ ሲሆን በእንግሊዘኛ እና በአረብኛ የሚነበብ ድረ ገጽም አለው።

ፌስቡክና ትዊተር እንዳሉት ከሆነ ድርጅቱ ከፍቶ የነበረው ዘመቻ በጣም አነስተኛ ውጤት ነበር ያገኘው።

ከሩስያ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ድርጅት በዚህ ዓመት አሜሪካ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑ የተሰማው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ጆ ባይደን የሚፋለሙበት ምርጫ ሊደረግ ሁለት ወር ብቻ በቀረው ወቅት ነው።

ፌስቡክና ትዊትር ከኤፍቢአይ ጋር አብረው ከሩስያ ጋር ንክኪ ያለውን ፒስዳታ የተሰኘ ድረገጽ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ግብረ ኃይል አቋቁመው ሲሰሩ ነበር ተብሏል።

ፌስቡክ በዚህ ዘመቻ 13 አካውንቶች፣ ሁለት ገጾችን ማስወገዱን ገልጾ " ትኩረታቸው በአሜሪካ የሚደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች ነበሩ" ካለ በኋላ ድርጅቱ ዩናይትድ ኪንግደም እና ግብጽ ላይም አይኑን መጣሉን አስታውቋል።

ነገር ግን የድርጅቱ ስኬት እዚህ ግባ የሚባል እንዳልነበር የገለፀው ፌስቡክ፣ 14 ሺህ ያህል አካውንቶች ከተወገዱት ገጾች መካከል አንዱን ወይንም ሁለቱንም ይከተሉ ነበር ብሏል።

የእንግሊዝኛ ድረ ገፁ 200 ተከታዮች ነበሩት ሲልም አክሏል።

የተሰረዙት አካውንቶች ሐሰተኛ ስም እና የፕሮፋይል ምስል ይጠቀሙ ነበር ተብሏል። ገጾቹ ላይ የሚጽፉት ለፒስዳታ ድረገጽ በነጻ የሚሰሩ ግለሰቦች ነበሩ።

ትዊተር በበኩሉ አምስት አካውንቶችን ማቋረጡን ገልጾ፣ ገጾቹ ከሩሲያ ጋር እንደሚገናኙ አስታውቋል።

በተጨማሪም በገጾቹ የሚወጡት መረጃዎች ይዘታቸው የወረደ መሆኑን ገልጾ፣ " በጣም በአነስተኛ ሰዎች ብቻ ይከተሏቸው፣ መረጃዎቻቸውንም ያዩ ያጋሩ ነበር" ሲል ገልጿል።

አይ አር ኤ በአሜሪካ የፍትህ ቢሮ የ2016 ምርጫ ላይ እጃቸውን አስገብተዋል ከተባሉ እና ከሩሲያ መንግሥት ጋር ግንኙነት አላቸው ከተባሉ ሶስት የሩሲያ ኩባንያዎች እንዲሁም 13 ሰዎች መካከል አንዱ ነው።