ዚምባብዌ፡ መንግሥት ነጭ ገበሬዎች መሬታቸውን መልሰው ማግኘት ይችላሉ ብሏል

ዚምባብዌ፡ መንግሥት ነጭ ገበሬዎች መሬታቸውን መልሰው ማግኘት ይችላሉ ብሏል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዚምባብዌ መንግሥት ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በመንግሥት በኃይል ከይዞታቸው እንዲነሱ ተደርገው የነበሩ ነጭ ገበሬዎች ማመልከቻ ለመንግሥት በማቅረብ ይዞታቸውን ማስመለስ ይችላሉ አለ።

ነጭ ገበሬዎቹ የተነጠቁት መሬት ሊመለስላቸው የማይቻል ከሆነ፤ በምትኩ ሌላ ስፍራ ላይ መሬት ይሰጣቸዋል ተብሏል።

እ.አ.አ. 2000 እና 2001 ላይ የወቅቱ የዚምባብዌ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ከነጭ ገበሬዎች መሬት ነጥቀው ለጥቁር ዚምባብዌውያን አድለው ነበር።

የፋይናንስ ሚንስትሩ መቱሊ ነኩቤ እና የመሬትና ግብርና ሚንስትሩ አንክሸስ ማሱካ በጋራ በሰጡት መግለጫ የቀደመው የዚምባብዌ መንግሥት ውሳኔ እንደሚቀለበስ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ከነጭ ገበሬዎች ተነጥቆ ጥቆሮችን የመሬት ባለቤት ያደረገው ሕግ ውድቅ ተደርጎ ጥቁሮችን ባለመብት ያደረገው የመሬት ባለቤትነት እውቅና ይሰረዛል ብለዋል ባለስልጣናቱ።

ነጭ ገበሬዎቹ ለመንግሥት አቤቱታ በማቅረብ የመሬት ይዞታቸውን ለ99 ዓመት መልሰው በሊዝ ማግኘት ይችላሉ ብለዋል ሚኒስትሮቹ።

ከ20 ዓመታት በፊት ተፈጻሚ በተደረገው አጨቃጫቂው የመሬት ሪፎርም ወደ 3500 የሚጠጉ ነጭ ገበሬዎችን ከመሬታቸው አፈናቅሎ ነበር።

ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ ብዙሃን የሆኑት ጥቁሮች መሬት ይገባቸዋል በማለት ከነጭ ገበሬዎች መሬት መንጠቃቸው ከምዕራባውያን አገራት ጋር አጋጭቷቸው ነበር።

1980 ላይ ዚምባበዌ አናሳ ከሆኑት የነጭ አገዛዝ ነጻነቷን አግኝታ ነበር። በወቅቱ ለእርሻ ምቹ የሆነው አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬት 4000 በሚሆኑ ነጭ ገበሬዎች ተይዞ ነበር።

ሙጋቤ ‘በቅኝ ግዛት የተበላሸውን የሃብት ክፍፍል ለማስተካከል’ በማለም ነበር የመሬት ይዞታዎችን ከነጭ ገበሬዎች የቀሙት።

ባለፈው ግንቦት ወር ላይ የፕሬዝደንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ መንግሥት በኃይል ከይዞታቸው ላይ እንዲፈናቀሉ ለተደረጉ ነጭ ገበሬዎች 3.5 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል መስማማቱ ይታወሳል።