ዚምባብዌ ለነጭ አርሶ አደሮች ካሳ ልትከፍል ወሰነች

አርሶ አደር በማሳ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Dan Kitwood

ዚምባብዌ መሬት ተወስዶብናል ላሉት ነጭ አርሶ አደሮች ካሳ ልትከፍል ነው

ዚምባብዌ የቅጭ ግዛት መገርሰስን እንዲሁም አገሪቷ ከተጫነባት ቀንበር ነፃ መውጣቷን ተከትሎ በኃይል ተነጥቆ የነበረውን መሬት ለጥቁሮች አከፋፍላለች።

ይህ መሬት በአናሳ ነጭ አርሶ አደሮች በኃይል ተይዞ የነበረ ነው።

ከሰሞኑ ደግሞ አገሪቷ ላከፋፈለችው መሬት ካሳ የሚሆን 3.5 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማምታለች። ይህ ገንዘብ መሬታቸው ተወሰደ ለተባሉት በሺዎች ለሚቆጠሩ ነጭ አርሶ አደሮች በካሳነት የሚሰጥ ይሆናል።

አገሪቷ በቀጥታ ለነዚህ ነጭ አርሶ አደሮች የምትከፍለው ገንዘብ ባይኖራትም ለረዥም ጊዜ በሚከፈል ቦንድና ከተለያዩ ለጋሽ አገራት በሚሰበሰብ ገንዘብም ካሳው ይሰጣል ተብሏል።

የአርሶ አደሮች ማህበር የካሳውን ሁኔታ በፀጋ እንደተቀበሉት ገልቨው፤ ካሳው ግን በቀጥታ ለመሬቱ ሳይሆን በዚህ ሂደት ለወደመው የእርሻ መሰረተ ልማት ግብዓት መሆን አለበት ሲል እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።

ዚምባብዌን ከእንግሊዝ ነጭ ቅጭ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ሲታገሉ የነበሩት ሮበርት ሙጋቤ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ነው 4 ሺህ 500 የሚጠጉ ነጭ አርሶ አደሮች መሬታቸው ተወስዷል።

ይህንንም መሬት 300 ሺህ ለሚጠጉ ጥቁር ቤተሰቦችም ተከፋፍሎ ነበር።

ሙጋቤ ከዘረኝነት አስተሳሰብ ነፃ የወጣ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በርካታ ተግባራት አከናውነዋል።

በጎርጎሳውያኑ 1992 ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመሬት ባለቤት መሆን የሚያስችል የመሬት ይዞታ ደንብ አስተዋወቁ። የደንቡ ዓላማ የነበረው ከ4500 በላይ በሚሆኑ ነጭ ገበሬዎች ተይዞ የነበረውን መሬት የዚምባብዌ ባለቤት ለሚሏት ጥቁሮች እንደገና ለማከፋፈል ያለመ ነበር።

በዚህ ምክንያት በ2000 መጀመሪያ አዲስ የተመሰረተው ለዲሞክራሲዊ ለውጥ ንቅናቄ [ሙቭመንት ፎር ዲሞክራሲ ቼንጅ] መሪ በነበሩት ሞርጋን ፅፋንጊራይ በሚመራው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ነበር።

ሙጋቤ ከአርሶ አደሮቹ ጎን ባለመቆማቸው የእንቅስቃሴው ደጋፊ ተደርገውም ይቆጠሩ ነበር። የቀድሞ ወታደሮች በነጮች ተይዞ የነበረውን መሬት የግላቸው ያደረጉ ሲሆን፤ በወቅቱም በርካታ ገበሬዎችና ጥቁር ሠራተኞች ተገድለዋል።