ኢራናዊው በ16 ዓመቱ 'ለፈጸመው ወንጀል' በ30 ዓመቱ በሞት ተቀጣ

ኢራን በምትፈጽመው የሞት ቅጣት ተደጋጋሚ ተቃውሞ ይሰነዘርባታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢራን በምትፈጽመው የሞት ቅጣት ተደጋጋሚ ተቃውሞ ይሰነዘርባታል

ኢራን ውስጥ አንድ ግለሰብ የ16 ዓመት ታዳጊ ሳለ ፈጽሞታል በተባለ ወንጀል ከበርካታ ዓመታት በኋላ የሞት ቅጣት ተፈጸመበት።

የተባበሩት መንግሥታት ይህ በግለሰቡ ላይ ተግባራዊ የሆነው የሞት ቅጣት ተገቢ አይደለም ሲል በመቃወም በኢራን ላይ ወቀሳው አሰምቷል።

በተባበሩት መንግሥት የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ እንዳስታወቀው የ30 ዓመቱ ሞሐመድ ሃሳን ረዚ ላይ በፍርድ ቤት ውሳኔ የሞት ቅጣቱ ተግባራዊ የተደረገው ትናንት ሐሙስ ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ሞሐመድ ሃሳን በአውሮፓውያኑ 2007 ላይ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው አንድ ግለሰብ ላይ በስለት ጥቃት ፈጽሟል ተብሎ ነበር።

የመብት ተሟጋቹ አክሎም በወቅቱ ታዳጊው በጫና ድርጊቱን ስለመፈጸሙ የእምነት ቃሉን እንዲሰጥ መደረጉን ገልጿል።

እንዲህ አይነት ግድያ በህጻናት መብት ላይ ከሚፈጸም ጥሰት ተለይቶ መታየት የለበትም ብሏል አምነስቲ ኢንተርናሽናል።

"አንድ ሰው ታዳጊ እያለ ፈጸመው ለተባለ ወንጀል ከዓመታት በኋላ ጠብቆ መቅጣት ሁሉንም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን የሚጥስና ህጻናት ወንጀል ከፈጸሙ መገደል የለባቸውም የሚለውን ሕግ የሚጣረስ ነው" ሲል መገልጫ አውጥቷል።

የሞሐመድ ሃሳን መገደልን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነሯ ሚሼል ማቼት የኢራንን ውሳኔ በጥብቅ እንደሚቃወሙ የሚገልጽ መግለጫ አውጥተዋል።

በመግለጫው ላይም ተጨማሪ ሦስት ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ታዳጊዎች በዚህ ዓመት ኢራን ውስጥ እንደተገደሉ ተገልጿል። በተጨማሪም 80 ሌሎች ህጻናት የሞት ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ ብሏል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደገለጸው ደግሞ ሞሐመድ ሃሳን የሞት ፍርድ ከተላለፈበት በኋላ ላለፉት 12 ዓመታት በእስር ያሳለፈ ሲሆን ወንጀለኛ መሆኑንም ያመነው በደረሰበት ድበደባና ማሰቃየት ነው ብሏል።