የስደተኞች ተቆርቋሪና የስኬት ተምሳሌቷ አጊቱ ጉደታ ማን ነበረች?

አጊቱ ከፍየሎቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አጊቱ ከፍየሎቿ ጋር

ማክሰኞ ዕለት በሰሜናዊ ጣሊያን ትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ ነዋሪ የነበረችው ታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት የአጊቱ ጉደታ ግድያን ተከትሎ በጣሊያን የኢትጵያ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተል ከባልደረቦቻቸው ጋር ወደ ስፍራው መሄዳቸውን ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል።

ኤምባሲው የአጊቱ ግድያ ከተሰማ በኋላ ተሰማውን ሐዘን ገልጾ ወንጀሉን በተመለከተም ከጣሊያን መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወሳል።

መስመር

በጣሊያን ውስጥ ከፍየል ወተት በምታዘጋጀው አይብ [ቺዝ] ታዋቂነት ያተረፈችው የስደተኛዋ ኢትዮጵያዊት የአጊቱ ጉደታ ግድያ በጣልያን ከባድ ድንጋጤን ከመፍጠሩ ባሻገር የዓለም መገናኛ ብዙሃን ዋነኛ ርዕስ ሆኗል።

በተለይም ለስደተኞች መብት በመቆም የምትታወቀው የአጊቱ መገደል ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ልብ ሰብሯል። በርካቶች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሀዘናቸውን እየገለጹም ነው።

በጣልያኗ ትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ፍራሲሎንጎ ትኖር የነበረው አጊቱ ቤቷ ውስጥ ነበር ተገድላ የተገኘችው።

ምርመራ እያደረገ እንደሆነ የገለጸው ፖሊስ እንዳለው፤ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ጭንቅላቷ ላይ ክፉኛ ተመትታ ጉዳት ደርሶባት አስከሬኗ የተገኘው ባለፈው ማከሰኞ ነበር።

የሞተችው ጭንቅላቷ ላይ በመዶሻ ተመታ ሊሆን እንደሚችልና በግድያው ተጠርጥሮ የተያዘ ጋናዊ ስደተኛ ለፖሊስ በሰጠው ቃል ወንጀሉን መፈጸሙን ማመኑም ተገልጿል።

የጣልያኑ ጋዜጣ ኮርየር ዴላ ሴራ እንደዘገበው አጊቱን የገደላት ሠራተኛዋ ጋናዊው ሱሌይማን አዳምስ 32 ዓመቱ ነው።

የግድያው ምክንያት ከክፍያ ጋር በተያያዘ የተፈጠረ አለመግባባት ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል።

የትሬንቲኖ ግዛት የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ሚካኤሌ ካፑርሶ "በአጊቱ እና ሱሌይማን መካከል ጸብ መኖሩን አናውቅም። ከዚህ ቀደም ቀጥራው አብሯት ሠርተዋል" ብለዋል።

ጨምረውም አጊቱ ከሁለት ወር በፊት በግድያው የተጠረጠረውን ሱሌይማን አብሯት እንዲሠራ እንደጠራችው ገልጸው፤ የአንድ ወር ደሞዝ አልተከፈለኝም በሚል አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር አስረድተዋል።

የግድያው ተጠርጣሪ አጊቱን ቢያንስ ሦስት ጊዜ በመዶሻ እንደተመታችና ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሰባት ማመኑንም ኮሎኔል ሚካኤሌ ገልጸዋል።

አጊቱ ማን ነበረች?

አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው አጊቱ ከአስር ዓመት በፊት ነበር በስደት ወደ ጣሊያን የሄደችው።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስትጨርስ ነጻ የትምህርት እድል አግኝታ በትሬንቲኖ ዩኒቨርስቲ ማኅበረሰብ ሳይንስን አጥንታ በዲግሪ ተመርቃለች።

ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ለጥቂት ጊዜ ከቆየች በኋላ እአአ 2010 ላይ ወደ ጣልያን ተመልሳ ሄዳ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቀች።

ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያካሄዱትን የመሬት ነጠቃ በመቃሟ የግድያ ዛቻ ይደርስባት ስለነበር ኢትዮጵያን ጥላ ለመሄዷ ምክንያት ነበር።

ከፍየል ወተት አይብ የማምረት ሐሳብን የወጠነችውም ወደ ጣልያን ካቀናች በኋላ ነው።

ከኢትዮጵያ ሸሽታ ጣልያን ውስጥ ጥገኝነት ከጠየቀች በኋላ የስደት ኑሮዋን የምትገፋበት መተዳደሪያ መፍጠር ነበረባት።

በዚህም በትሬንቲኖ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ፍየሎችን ማርባትና ልዩ ልዩ የወተት ተዋጽኦ ማምረት ከጀመረችም ዓመታት ተቆጥረዋል።

በምትኖርበት አካባቢ ባሉ ጣልያናውያን እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በስደት ወደ ጣልያን በሄዱ ሰዎች ዘንድም ታዋቂና ተወዳጅ ነበረች - አጊቱ።

አጊቱ ጉደታ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Embassy in Rome

አጊቱና የፍየል እርባታ

ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገችው ቆይታ እንስሳትን ማርባት በቤተሰቧ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረ ልማድ እንደሆነ ተናግራለች።

በተጨማሪም ቀደም ሲል ዋነኛ ትኩረታቸውን በአርብቶ አደሮች ላይ ባደረጉ በዘላቂ ግብርና ፕሮጀክቶች ላይ በመስራት ልምድ የነበራት አጊቱ በእንስሳት እርባታ ሥራዋ ስኬት የእራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደነበረው ከዚህ በፊት ተናግራ ነበር።

ጣልያን ውስጥ ከፍየል ወተት አይብ ማምረት ስትጀምር ለበርካታ አፍሪካውያን የሥራ እድል ፈጥራለች። ከዚህ ባሻገርም ዘረኛነትን በመጋፈጥ እንዲሁም ለስደተኞች መብት በመቆም ትታወቃለች።

ፍየሎች ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚያስደስታት በተለያዩ ቃለ መጠይቆች ተናግራለች።

ጣልያን ውስጥ ጥቅም ላይ ያልዋለ የእርባታ መሬት ስታገኝ አገር በቀል ፍየሎችን ለማርባት ወሰነች።

ፔታታሞኒኪና የሚል መጠሪያ ያላቸው እና ዝርያቸው ሊጠፋ የነበሩ ፍየሎችን ማርባት የጀመረቸው አጊቱ በመነሻዋ ላይ 15 ፍየሎች ብቻ ነበሯት።

በጊዜ ሂደት ወደ 180 የሚደርሱ ፍየሎችን ማርባት ስትችል፤ የፍሎቹን ወተት በመጠቀም ታዋቂነትን ያተረፈላትን ተወዳጅ አይብ ማምረት ጀመረች።

በምትኖርበት አካባቢ ፍየሎቹን ለማሳደግ ስለሚመችና አገር በቀል ስለሆኑ እንደመረጠቻቸው ተናግራ ነበር።

በፍየል እርባታዋና በአይብ ምርት ሥራዋ ውስጥ ከምትቀጥራቸው ሠራተኞች መካከል አብዛኞቹ የሥራ ዕድል ያላነኙ ስደተኞች ናቸው።

ጣልያን ውስጥ ስለተማረች ከመኖሪያ ፍቃድ ጋር የተያያዙ ሰነዶች እንዲሁም ትሬንቲኖ ውስጥ ጓደኞችም ነበሯት።

ተወዳጁ የአይብ ምርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተወዳጁ የአይብ ምርት

ከፍየል ወተት ስለሚሠራ አይብ ለመማርና አብረዋት ለመሥራት የሚሄዱም ብዙ ናቸው። እሷም የምትወደውን ሙያ ለሠራተኞቿ ከማስተማር ወደኋላ አትልም።

ሙያውን ለማዳበር በፍየል አይብ ወደምትታወቀው ፈረንሳይ ሄዳ ስለ አይብ አሠራር ተምራለች።

ወደ 15 የሚደርሱ የአይብ አይነቶች ለደንበኞቿ ታቀርባለች። በሥራዋ የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውላታል።

በሚላን ኤክስፖ ላይ የምትኖርበትን ግዛት ወክሎ የቀረበውም የእሷ የአይብ ምርት ነበር።

በምትኖርበት ግዛት ከፍየል ወተት የሚሠራ አይብ ሙያ ውስጥ ማንም አልነበረም ማለት ይቻላል።

አጊቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ከተለያየ አካባቢ ለሚሄዱም ለዓመታት አይብ አቅርባለች። ከፍየል ወተት የሚሠራ ተፈጥሯዊ መዋዋቢያ ታመርታለች። ቱሪስቶችን የፍየል መንጋም ታስጎበኛለች።

የዘረኝነት ፈተና

ጣሊያን ከጀርመን ጋር በምትዋሰንበት ተራራማዋ ትሬንቲኖ ውስጥ ለዓመታት የኖረችው አጊቱ፤ ዘረኛነት ላይ የተመሠረቱ ጥቃቶች ያጋጥሟት እንደነበር ለፖሊስ አመልክታለች።

"አስቀያሚ ጥቁር እያሉ ይሰድቡኛል፤ ያለሁበትም ቦታ አገሬ እንዳልሆነ ይነግሩኛል" በማለት ያገጠሟትን የዘረኛነት ጥቃቶች ስትገልጽ ነበር።

አጊቱ የሚገጥማትን የዘረኝነት ጥቃት ይፋ ባወጣችበት ጊዜ የግዛቲቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኡጎ ሮሲ ድርጊቱን ተቃውመው ከጎኗ ቆመው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ "አጊቱ ስደተኛ ሆና የእንስሳት እርባታ ሥራዋን በግዛታችን ውስጥ ማከናወን መጀመሯ የትሬንቲኖን እንግዳ ተቀባይነትና ደጋፊነትን ያሳያል" ብለው ነበር።

አጊቱ በተለይም ለስደተኞች የአዲስ ሕይወት ተስፋና ተምሳሌት ነበረች። በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት [ጃንዋሪ 1/2021] አርብ ዕለት 43 ዓመት ይሆናት ነበር።