ሶሪያ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 28 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በምሥራቃዊ ሶሪያ በአውቶብሶች ላይ በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት ቢያንስ 28 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረና ሁሉም ወታደሮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገለጸ።
የሶሪያ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደገለጸው አውቶብሶቹ ዴር አል ዘር ተብሎ በሚታወቀው ግዛት ረቡዕ እለት ነው ኢላማ የተደረጉት። በጥቃቱም በርካታ ዜጎች ተገድለዋል ብሏል ጣቢያው።
ነገር ግን አንዳንድ ምንጮችና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አውቶብሱ ውስጥ ወታደሮች እንደነበሩ እና የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል አስታውቀዋል።
ከጥቃቱ በኋላ ወዲያው ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን አልነበረም።
መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሶሪያ ሰብአዊ መብቶች ተቆጣጣሪ ድርጅት ጥቃቱን የፈጸመው ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) እንደሆነ በመግለጽ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 37 ነው ብሏል።
ድርጅቱ በቦታው ላይ የነበሩ ምንጮችን በመጥቀስ ''ጥቃቱ በተቀናጀ መልኩ በኢስላሚክ ስቴት አባላት የተካሄደ ነው። መንግስትን የሚደግፉ ታጣቂዎችና ወታደሮችን የጫኑ ሶስት አውቶብሶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል'' ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ሌሎች ምንጮች ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሲናገሩ አውቶብሶቹ የሶሪያ ወታደሮችን ጭነው ነበር።
የአይኤስ ተዋጊዎች እና ለሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ መንግስት ታማኝ የሆኑ ወታደሮች በጥንታዊቷ ፓልሚራ ከተማ አካባቢ በተደጋጋሚ ይዋጋሉ።
በአውሮፓውያኑ 2014 አይኤስ በሚሊየኖች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ ከባድ አስተዳደራዊ መዋቅር ጭኖ የነበረ ሲሆን በአንድ ወቅት 88 ሺ ስኩዌር ኪሎሜትር የሚደርስ ድንበር ያስተዳድር ነበር።
ከአምስት ዓመታት ውጊያ በኋላ የአካባቢው ወታደሮች በአሜሪካ በመታገዝ ቀስ በቀስ በአይኤስ ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን ማስለቀቅ ችለዋል።
በዚህም ምክንያት አይኤስ የሚያስተዳድረው ሰፊ ግዛት እንደሌለው ታውጆ የነበረ ሲሆን 2019 ላይ ሶሪያ እና ኢራቅ ላይ በዚህ ረገድ ተሸንፏል ተብሎ ነበር።
ነገር ግን አሁንም ድረስ የቡድን እንቅስቃሴ ሶሪያን ያምሳታል።












