አሜሪካን ለእስራኤል ሲሰልል የነበረው ከ30 ዓመት እስር በኋላ ቴል አቪቭ ገባ

ጆናታን ፖላርድ

የፎቶው ባለመብት, ISRAEL HAYOM VIA REUTERS

ጆናታን ፖላርድ የተባለው አሜሪካን ለእስራኤል ሲሰልል የነበረው ግለሰብ፤ ከ30 ዓመታት እስር ተለቆ እስራኤል፣ ቴላ ቪቭ ገባ።

የ66 ዓመቱ ግለሰብ ለአንድ ወር ተጥሎበት የነበረው የጉዞ እገዳ ከተነሳ በኋላ ከባለቤቱ ኤስተር ጋር ወደ እስራኤል አቅንቷል።

አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተቀበሏቸው ሲሆን “አሁን አገራችሁ ናችሁ” ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትሩ የእስራኤል ብሔራዊ መታወቂያ ሰጥተዋቸዋል።

ጆናታን የታሰረው እአአ በ1985 ነበር። የአሜሪካን ሚስጥር ለእስራኤል መስረቁን አምኖ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት ነበር።

አሜሪካ ከአጋሯ እስራኤል መረጃ መደበቋ አስቆጥቶት እንደነበር ተናግሯል። መጀመሪያ ላይ ጆናታን ይሰልልላት እንደነበረ እስራኤል አላመነችም። ከሕገ ወጥ ባለሥልጣኖች ጋር እንደሚሠራም ተነግሮ ነበር

1995 ላይ ግን እስራኤል ዜግነት ሰጠችው። 3 ዓመት ቆይታ ደግሟ ሰላይ እንደሆነ አመነች። ከእስር እንዲለቀቅ እስራኤል ብትጠይቅም ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች እስከ 2015 ድረስ አልፈቀዱም።

2015 ላይ ሲለቀቅ፤ ቢያንስ ለአምስት ዓመት ያለ ፍቃድ ከአሜሪካ ውጪ መጓዝ እንደማይችል ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦ ነው። ባለፈው ወር የአሜሪካ የፍትሕ ተቋም የጉዞ ክልከላው እንደተነሳለትና እስራኤል መሄድ እንደሚችል አስታውቋል።

አሜሪካዊው ቢልየነር ሸልደን አደልሰን እና ባለቤቱ ሚርያም ባመቻቹት የግል ጀት ከኒው ጀርሲ እስራኤል በሯል።

ከባለቤቱ ጋር እስራኤል እንደደረሱ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የተቀበሏቸውደ ቤንያሚን ኔታንያሁ “እንኳን ደህና መጣችሁ። በስተመጨረሻ አገራችሁ መምጣታችሁ መልካም ነው። እዚህ በነጻነትና በሀሴት አዲስ ሕይወት መጀመር ትችላላችሁ” ብለዋል።

ጥንዶቹ እስራኤል ሲደርሱ ተንበርክከው መሬቱን ስመው የአይሁድ እምነት ፀሎት አድርሰዋል።

ጆናታን “ከ35 ዓመት በኋላ አገራችን መመለስ እጅግ ያስደስታል። ሕዝቡና ጠቅላይ ሚንስትሩ አገራችን እንድንገባ ስላደረጉን እናመሰግናለን። በአገራችን እና በመሪያችን እንኮራለን። ውጤታማ ዜጎች ለመሆን ቆርጠን ተነስተናል” ሲል ስሜቱን ገልጿል።

ለቀጣይ ሁለት ሳምንታት እየሩሳሌም ውስጥ ባለ አፓርትመንት ራሳቸውን ለይተው ያቆያሉ።

እስራኤል ሃዮም የተባለው ጋዜጣ ባለቤት ሚርያም፤ ጆናታን ሞቅ ያለ አቀባበል እንዲደረግለት ጠይቃለች። “እስራኤል ውለታው አለባት። ተጎድቶ እንደመጣ ወታደር አገሪቱ የሚገባውን ሁሉ ልታመቻችለት ይገባል” ብላለች።

1998 ላይ ከአሶሽየትድ ፕረስ ጋር በነበረው ቆይታ፤ ጆናታን ለስለላ የከፈለው መስዋዕትነትና ያገኘው ዋጋ እንደማይመጣጠኑ ተናግሮ ነበር።

“ምንም ውጤት አላገኘሁም። ሁለት አገሮች ለማገልገል ሞክሬያለሁ። ያ ደግሞ አይሠራም” ብሎ ነበር በቃለ ምልልሱ።